ሲዳማ ቡና ኬንያዊ አማካይ አስፈርሟል

  ዝውውር | 19-01-2009 

ሲዳማ ቡና ኬንያዊውን የአማካይ ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ሰንደይ ሙቱኩ የስፖርትፔሳ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ከሆነው ካካሜጋ ሆምቦይዝ ክለብ አስፈርሟል።

ተጫዋቹ ባለፈው ቅዳሜ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ እሁድ ዕለት የኢትዮጵያ የክረምቱ የዝውውር መስኮት ከመዘጋቱ በፊት ለደቡቡ ክለብ ፊርማውን አኑሯል። በስምምነቱ መሠረት ሰንደይ ሙቱቱ በሲዳማ የአንድ ዓመት ቆይታ የሚኖረው ሲሆን ሲዳማ ቡና ለኬንያው ክለብ የ600,000 ሺሊንግ (130,000 ብር) የዝውውር ሂሳብ ከፍሏል።

የካካሜጋ ሆምቦይዝ ክለብ ሊቀመንበር ክሌኦፓስ ሺማንዩላ ዝውውሩን ለኬንያ የሚዲያ ተቋማት ይፋ ያደረጉ ሲሆን በሰጡት አስተያየት የቀድሞ ተጫዋቻቸው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውጤታማ እንደሚሆን ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል ” ሰንደይ ሙቱኩ ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሏል። ተጫዋቹ በተሻለ ወደሚጠቀምበት ክለብ በመሄዱ ደስተኛ ነን። ለሲዳማ ቡና እጅግ ጠቃሚ ተጫዋች ይሆናል ብዬ አስባለሁ፤”

picsart_1475147152460

ሙቱኩ የተጫዋችነት ህይወቱን በኬንያ 3ኛ ዲቪዝዮን በሚጫወተው ያታ ኮምባይንድ ክለብ ነበር የጀመረው። እ.ኤ.አ. በ2015 በ2ኛ ዲቪዝዮኑ ሻባና እግርኳስ ክለብ ከተጫወተ በኋላ ወደ ኬንያ ፕሪምየር ሊግ ያደገውን ካካሜጋ ሆምቦይዝ ተቀላቅሏል። ከአማካይነት በተጨማሪ በመሃል ተከላካይነት መጫወት የሚችለው ሙቱኩ ዘንድሮ ክለቡን በአምበልነት እየመራ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ማሳየት የቻለ ሲሆን 3 ግቦችንም በስሙ ማስመዝገብ ችሏል።

Leave a Reply