” ሃገራትን እና እግርኳሳቸውን የመናቅ አስተሳሰብ መቆም አለበት” ፍቅሩ ተፈራ

  ኢትዮጵያውያን በውጪ | 19-01-2009  

የቀድሞው የአዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ፍቅሩ ተፈራ በባንግላዴሽ ፕሪምየር ሊግ ከሚሳተፈው ሼኢክ ሩሴል ክለብ ጋር ያለውን ኮንትራት ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመልሷል።

ተጫዋቹ ለጊዜው የትኛውንም ክለብ መቀላቀል ባይችልም የደቡብ አፍሪካ የዝውውር መስኮት ጥር ላይ በድጋሚ ሲከፈት ወደሜዳ የመመለስ እቅድ እንዳለው ተናግሯል። “ወደ ደቡብ አፍሪካ የተመለስኩት ቤተሰቤ እዚህ ስለሚኖር ነው። ለ7 ወራት ያህል በባንግላዴሽ ስጫወት ከልጆቼ ርቄ ስለነበር ከነሱ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ስል ነው የመጣሁት። በአሁኑ ሰዓት የአሠልጣኝነት ኮርሶችን ለመውሰድ ዕድሉን በማመቻቸት ላይ ነኝ። ነገርግን ቀጣዩ የዝውውር መስኮት በሚከፈትበት ጊዜ ክለብ በመቀላቀል የእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወቴን ለመቀጠል እፈልጋለሁ፤ ከሁለት ክለቦች ጋርም ይህን በተመለከተ እየተነጋገርኩኝ ነው።” ብሏል፡፡

ፍቅሩ ተፈራ ባለፉት የውድድር ዘመናት እንደ ባንግላዴሽ እና ህንድ የመሳሰሉ በእግርኳሱ ዝቅተኛ ግምት በሚሰጣቸው ሃገራት ሄዶ ስለመጫወቱ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ ከገቢ ተጠቃሚነት አንፃር ወደነዚህ ሀገራት መጓዝ ውድቀት እንዳልሆነ ገልጿል፡፡

“እግርኳስን ስንጫወት እንደልጅነታችን ለኳሱ ባለን ፍቅር ብቻ ተገፍተን አይደለም፤ ቤተሰባችንን ማስተዳደር የሚያስችለን ገንዘብ እንዲከፈለን ነው እንጂ። እግርኳስ አሁን በዓለም ዙሪያ የተስፋፋ ስፖርት ነው። በማንኛውም አገር ያለ ክለብ ለአንድ ተጫዋች በቂ ገንዘብ ያለው ኮንትራት ካቀረበ እና በክፍያው ከተስማሙ ወደዚያ ሃገር ሄዶ መጫወት እንዳለበት አምናለሁ።

“ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ህንድ ሄዶ እግርኳስ መጫወት በብዙዎች ዘንድ የማይታሰብ ነበር። አሁን ግን በርካታ ተጫዋቾች ወደዚያ ሄደው ለመጫወት በማሰብ ምክር ፈልገው ይደውሉልኛል። ሃገራትን እና እግርኳሳቸውን የመናቅ አስተሳሰብ መቆም ያለበት ነገር ነው። እኔ በተጫወትኩባቸው ሃገራት ሁሉ ሄዶ መሄድ የሚፈልግ ተጫዋች ጥሩ ኮንትራት ከቀረበላቸው እንዲሄዱ እመክራለሁ።”

ፍቅሩ ተፈራ በእግርኳስ ህይወቱ በ7 ሃገራት በሚገኙ ከ15 በላይ ክለቦች ተጫውቷል። የደቡብ አፍሪካዎቹ ሱፐርስፖርት እና ኦርላንዶ ፓይሬትስ፣ የፊንላንዱ ኬዩፒኤስ እና የቼክ ሪፐብሊኩ ምላዳ ቦሌስላቭ ፍቅሩ ተጫውቶ ካሳለፈባቸው ክለቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *