የአዲስ አበባ ዋንጫ የምድብ ድልድል ይፋ ሆኗል

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው የአዲስ አበባ ዋንጫ የእጣ  ማውጣት ስነስርዓት ዛሬ ከቀኑ 5:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል ተደርጓል፡፡

ስምንት ክለቦች እንደሚሳተፉበት በተገለፀው ይህ ውድድር ስድስቱን የአዲስ አበባ ክለቦች እና ሁለት ተጋባዥ ክለቦችን በመጨመር እንደሚከከናወን ሲታወቅ ከአዳማ ከተማ ውጭ ሌላኛው ተጋባዥ ቡድን ኬሲሲኤ (ካምፓላ ካፒታል ሲቲ አውቶሪቲ) እንደሆነም ከእጣ ማውጣቱ በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አማረ ማሞ የውድድሩ ዋና አላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሆነ ገልጸው የዚህን አመት ውድድር ምን ለየት እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡

“የ2009 የአዲስ አበባ ዋንጫ ከሌላው ጊዜ በተለየ አዲስ የአዲስ አበባ ክለብ ማግኘታችን ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ በደንብ የሚታወቀውን ኬሲሲኤ ወደ ሃገራችን በመጋበዝ ውድድሩን እንዲያደምቅልን ማድረጋችን ከሌለው ጊዜ ለየት ያደርገዋል”

ኢትዮጵያ ቡና በውድድሩ ላይ ያልተሳተፈበትን ምክንያት የተጠየቁት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት “በኛ በኩል እንደ ማንኛውም ክለብ እንዲሳተፍ ደብዳቤ ከአንድም ሶስት ጊዜ ልከናል፡፡ ነገር ግን ከክለቡ ይፋዊ ምላሽ ባለማግኘታችን ወደ ሁለተኛ እቅዳችን ሄደናል፡፡ ወደፊት እንደ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ አድርገን የሚወሰኑ ውሳኔዎችን እናሳውቃለን፡፡ ነገር ግን አሁንም ፌደሬሽናችን ከክለቡ ጋር በጠረቤዛ ዙሪያ ለመነጋገር ፍቃደኞች ነን”ብለዋል፡፡

በውድድሩ ደምብ ላይ ብዙም አዲስ ነገር እንደሌለ የተገለጸ ሲሆን ውድድሩን በቁጥራዊ መረጃ ሁሉንም ጨዋታዎች እንዲተነትን ከአር ኤንድ ዲ ግሩፕ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን እና የስፖርት ቤተሰቡ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ እንዲያገኝ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ይፋዊ የኦንላይን ሚዲያ አጋር እንደሆነም በመግለጫው ላይ አስታውቋል፡፡

picsart_1475324140933

ከጋዜጣዊ መግለጫው በኃላ በተከናወነው የእጣ ማውጣት ስነስርዓት አንጋፋ የእግር ኳስ ሰዎች በቦታው በመገኘት የእጣ ማውጣት ስነስርዓቱን አከናውነዋል፡፡

በእጣውም መሰረት በምድብ ሀ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ኬሲሲኤ ፣ መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲደለደሉ በምድብ ለ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ደደቢት ፣ አዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ተደልድለዋል፡፡

በፕሮግራሙ መሰረት ቅዳሜ መስከረም 28 በሚደረገው የመክፈቻ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኬሲሲኤ ከመከላከያ ከምድብ ሀ እንደሚጫወቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በምድብ ለ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዲስ አበባ ከነማ እንዲሁም ደደቢት ከአዳማ ከነማ እሁድ መስከረም 29  ይደረጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *