የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ወደ ማዳጋስካር የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ለማለፍ ፈታኝ 90 ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውታል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ባማኮ ላይ 2-0 ተሸንፎ የተመለሰው ከ17 አመት በታች ቡድናችን ለመልሱ ጨዋታ በአዲስ አበባ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ቡድናችን ከአዲስ አበባን አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ለመጠቀም በማሰብም ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታድየም ላይ ለማድረግ ወስኗል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አሰትያየት ለመልሱ ጨዋታ መልካም ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
” ጥሩ ዝግጅት ስናደርግ ነበር፡፡ ከማክሰኞ ጀምሮ ጨዋታውን በምናደርግበት አዲስ አበባ ስታድየም ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ማሊን አሸንፈን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ተዘጋጅተናል፡፡ በነገው ጨዋታ አጥቅተን በመጫወት ውጤቱን መቀልበስ ይገባናል፡፡ ይህ ማለት ግን መከላከሉን አንዘነጋለን ማለት አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡
ከጉዳት ጋር በተያያዘ ምንም ጉዳት የሌለ ሲሆን ሁሉም ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ብቁ ናቸው፡፡ የቡድኑ የፈጠራ ምንጭ የሆነው የአጥቂ አማካዩ ሚኪያስ መኮንን በ2 ቢጫ ምክንያት የነገው የመልስ ጨዋታ የሚያመልጠው መሆኑ ከኢትዮጵያ በኩል የሚጠቀስ ብቸኛው ስጋት ነው፡፡
የወቅቱ የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ቻምፒዮን የማሊ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን የልኡካን ቡድን በሃገሪቱ ስፖርት ኮሚሽን ክሚሽነር ሴኮ ሲይላ እየተመሩ ትላንት አዲስ አበባ የደረሱ ሲሆን በዛሬው እለት ከ10:00 ጀምሮ ጨዋታው በሚካሄድበት አዲስ አበባ ስታድየም ልምምዳቸውን አከናውነዋል፡፡
የነገው የኢትዮጵያ እና የማሊ ጨዋታ 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲካሄድ የኒጀር ዳኞች ጨዋታውን ይመሩታል፡፡ ማሊ የ2-0 መሪነት ይዛ በምትገባበት ጨዋታ በድምር ውጤት የበላይ የሚሆነው ቡድን የአፍሪካዋ ትልቅ ደሴት ማዳጋስካር በአዲሱ የፈረንጆች አመት ለምታስተናግደው የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ማለፉን ያረገግጣል፡፡