ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2006 የአአ ከተማ ዋንጫ ሻምፒዮን !

ለስምንተኛ ጊዜ የተካሄደው የዋና ከተማዋ ዋንጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሁሉንም ግጥሚያዎች ያሸነፈው ቅዱስ ጊርጊስ እና ከምድቡ ቅዱስ ጊዮርጊስን ተከትሎ ያለፈው ኢትዮጵያ መድን በፍፃሜው ተገናኝተው ለዋንጫው ከፍተኛ ግምትን ያገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደተገመተው የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ ከረጅም ጊዜ ጉዳት አገግሞ በሲቲ ካፑ ወደ ጨዋታ የተመለሰው ፍፁም ገብረ ማርያም ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ መድንን 1-0 በማሸነፍ ለ4ኛ ጊዜ የዋና ከተማዋ ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል፡፡

ወጣት ተጫዋቾቻቸውን ከተጠባባቂ ተጫዋቾቻቸው ጋር በማዋኃድ ይዘውት የቀረቡት ፈረሰኞቹ ሁሉንም ጨዋታ አሸንፈው ለዋንጫ ድል በቅተዋል፡፡ ዘንድሮ በሊጉ ፣ በጥሎ ማለፉ እና በሲቲ ካፑ ባደረጓቸው 12 ጨዋታዎችም 1 ጊዜ በመለያ ምቶች ሽንፈት ሲደርስባቸው ቀሪዎቹን 11 ተከታታይ ግጥሚያዎች በድል ተወጠዋል፡፡

በእለቱ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ፍፁም በ6 ግቦች የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ ሲያጠናቅቅ መድንን ለፍፃሜው ያበቁት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡

ትላንት ለደረጃ ኢትዮጵያ ቡና እና ንግድ ባንክ ባደረጉት ጨዋታ በመደበኛው ሰአት 0-0 ሲለያዩ በመለያ ምቶች ኢትዮጵያ ቡና 5-4 አሸንፎ የ3ና ደረጃን አግኝቷል፡፡

{jcomments on}