በአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ማሊን የገጠመው የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በድምር ውጤት 4-1 ተረትቶ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡
በመጀመርያው ጨዋተ ባማኮ ላይ 2-0 የተሸነፈችው ኢትዮጵያ ለማለፍ ከ2 ግብ በላይ ማስቆጠርን አልማ ወደ ሜዳ ብትገባም 2-1 ተሸንፋለች፡፡
ማሊዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ለማስቆጠር የፈጀባቸው 3 ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ሲቢሪ ኬይታ በኢትዮጵያ የግብ ክልል የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሯል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኀላ አመዛኙ የመጀመርያ አጋማሽ ደቂቃዎችን ማሊዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን ኢትዮጵያዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር የሚያበቃ ተነሳሽነት እና የማጥቃት እንቅስቃሴ ጎድሏቸው ታይቷል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ ኳስ መሞከር ሳይችሉም ቀርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ተነቃቅቶ የገባው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ የተንቀሳቀሰ ሲሆን የግብ እድሎችንም መፍጠር ችሏል፡፡
በ72ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ፋሲል አበባየሁ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን አቻ አድርጓል፡፡ ግቡን ተከትሎ ማሊዎች ኳስ በመቆጣጠር ጨዋታውን ያረጋጉት ሲሆን 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨማሪው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ተቀይሮ የገባው ማሃማኒ ቱሬ የማሊን አሸናፊነት ያረጋገጠች ግብ አስቆጥሯል፡፡ ጨዋታውም በማሊ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የ2015 የውድድሩ አሸናፊ ማሊ በድምር ውጤት 4-1 በማሸነፍ ወደ 2017 የማዳጋስካር የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ማለፍ ችላለች፡፡