ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ መድን

የአአ ከተማ ዋንጫ ዛሬ ይፈፀማል

ከጥር 4 ጀምሮ ሲካሄድ የሰነበተው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬ 10 ሰአት ላይ ይፈፀማል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናን በሰፊ ልዩነት ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጥሎ የመጣው ኢትዮጵያ መድን በሚያደርጉት የፍፃሜ ጨዋታ ፈረሰኞቹ ለ4ኛ ድል ሰማያዊዎቹ ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ ድል ይፋለማሉ፡፡

የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጠባባቂ እና ወጣት ተጫዋቾቹ የተጠቀመ ሲሆን አስከ ፍፃሜው ባደረገው ጉዞም ፈተና አልደረሰበትም፡፡ ምድቡን በበላይነት ሲያጠናቅቅ በግማሽ ፍፃሜውም ኢትዮጵያ ቡናን በቀላሉ አሸንፏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን ተከትሎ የምድቡ 2ኛ ሆኖ ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀለው መድን ንግድ ባንክን 1-0 አሸንፎ ወደ ፍፃሜው አልፏል፡፡

በ2001ዱ ፍፃሜ የመብራት ኃይል አሰልጣኝ ሆነው በመለያ ምቶች ቅዱስ ጊዮርጊስን ያሸነፉት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በከተማው ዋንጫ ፍፃሜ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለ2ኛ ጊዜ ይገጥማሉ፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የቀድሞ የአስራት ተጫዋቾች የነበሩት ዘሪሁን ሸንገታ እና ፋሲል ተካልኝ ዛሬ በአሰልጣኝነት አስራት ኃይሌን ይገጥማሉ፡፡

የፍፃሜው ጨዋታ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ የስፖርት ጋዜጠኞች ከ አርቲስቶች የሚጫወቱ ሲሆን በደጋፊዎች ድምፅ የሚመረጥ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋችም ይመረጣል፡፡

ትላንት ለደረጃ ኢትዮጵያ ቡና እና ንግድ ባንክ ባደረጉት ጨዋታ በመደበኛው ሰአት 0-0 ሲለያዩ በመለያ ምቶች ኢትዮጵያ ቡና 5-4 አሸንፎ የ3ና ደረጃን አግኝቷል፡፡

ያጋሩ