አዲስ ግደይ ደምቆ በዋለበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና የደቡብ ካስቴል ዋንጫ አሸናፊ ሆነ

የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ዛሬ ሲጠናቀቅ ሲዳማ ቡና አርባምንጭ ከተማን 3-1 በማሸነፍ ቻምፒየዮን ሆኗል፡፡ አዲስ ግደይ የጥምር ክብር ባለቤት ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ውድድሩን በ3ኝነት አጠናቋል፡፡

07:00 ላይ ለ3ኛ ደረጃ በተደረገው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 በመርታት 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡

ፍቃዱ ወርቁ በ6ኛው እንዲሁም ቴዎድሮስ ሁሴን በ37ኛው ደቂቃ የድሬዳዋን ግቦች ሲያስቆጥሩ ሳሙኤል ሳኑሚ በ56ኛው ደቂቃ የቡናን ግብ አስቆጥሯል፡፡

09:30 ላይ የተካሄደው የአርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ የሞቀ የደጋፊዎች ድባብ ፣ የአዲስ ግደይ አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት እና ማራኪ ፉክክር ታይቶበት በሲዳማ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት አርባምንጭ ከተማዎች ሲሆኑ በ6ኛው ደቂቃ በክረምቱ ክለቡን የተቀላቀለው ወንድሜነህ ዘሪሁን አዞዎቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ሆኖም የአርባምንጭ መሪነት ከ1 ደቂቃ መዝለል አልቻለም፡፡ ከመሃል ሜዳ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ አዲስ ግደይ በአግባቡ ተቆጣጥሮ በምርጥ አጨራረስ ሲዳማን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

ከእረፍት መልስ የግብ እድል በመፍጠሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማዎች አዲስ ግደይ በ46ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው ተጨማሪ ግቦች 3-1 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ አዲስ በተለይም ሐት-ትሪክ የሰራበትን ግብ በአክሮባቲክ ምት ያስቆጠረበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የአዲስ ግደይ የአጨራረስ ብቃት ፣ ፍጥነት እና ክህሎት የኢትዮጵያ ቀጣዩ ምርጥ ተጫዋች እንደሚሆን ያሳየ ነበር፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተካሄደው የሽልማት ስነ ስርአት ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እና ለተሳታፊ ክለቦች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

picsart_1476546799430

የውድድሩ ኮከቦች

ኮከብ ተጫዋች – አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)

ኮከብ ግብ አስቆጣሪ – አዲስ ግደይ (4 ግቦች)

ኮከብ አሰልጣኝ – አለማየሁ አባይነህ (ሲዳማ ቡና)

ኮከብ ግብ ጠባቂ – ዮሀሃንስ በዛብህ (ኢትዮጵያ ቡና)

ኮከብ ዋና ዳኛ – ፌዴራል አርቢቴር ብርሃኑ

ኮከብ ረዳት ዳኛ – ኢንተርናሽናል አርቢቴር ወይንሸት አበራ

picsart_1476548456315 picsart_1476547013387 picsart_1476546862767



ውድድሩን የተመለከቱ ዘገባዎች ከስፍራው እንድናቀርብ የተባበረን እና በሆቴል በመልካም መስተንግዶ ድጋፍ ላደረገልን ባለ አራት ኮከቡ ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ምስጋና እናቀርባለን፡፡

picsart_1475599616679

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *