ቻምፒየንስ ሊግ፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የአፍሪካ ሻምፒዮን ለመሆን ተቃርቧል

የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ቅዳሜ በፕሪቶሪያ ተደርጎ የአምስት ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ ዛማሌክ በማሜሎዲ ሰንዳውንስ 3-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ በዘንድሮ የቻምፒየስ ሊግ ብቻ ለሶስተኛ ግዜ የተገናኙ ሲሆን ሶስቱንም ጨዋታዎች በበላይነት የጨረሱት ብራዚሎቹ ናቸው፡
በሞሰስ ሞርፒ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሰንዳውስ በአንቶኒ ላፎር ግብ ቀዳሚ ሲሆን ቲቦጎ ላንገርማን ልዩነቱን ወደ ሁለት ያሰፋበትን ግብ በመጀመሪያው አጋማሽ ከግራ መስመር በድንቅ ሁኔታ አስቆጥሯል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የዛማሌኩ ተከላካይ ኢስላም ገማል በራሱ ግብ ላይ ሶስተኛው አስቆጥሮ ውጤቱ ወደ ሶስት ሰፍቷል፡፡የዛማሌክ የኋላ መስመር በተከታታይ ባደረጋቸው ሁለት የቻምፒየንስ ሊጉ ከሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን አስተናግዷል፡፡

ከወዲሁ ለመልሱ ጨዋታ ከሶስት ግብ በላይ በሆነ ውጤት የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ የገባው የካይሮው ሃያል ክለብ ዛማሌክ ለስድስተኛ ግዜ የቻምፒየንስ ሊጉን ዋንጫ የማንሳት ተስፋው በጣም የጠበበ ይመስላል፡፡
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከኦርላንዶ ፓይሬትስ በመቀጠል የቻምፒየንስ ሊጉን ዋንጫ ያነሳ ሁለተኛው የደቡብ አፍሪካ ክለብ የመሆኑ ተስፋ የለመለመ ነው፡፡ በ2013 ኦርላንዶ ፖይሬትስ በአል አሃሊ ተሸንፎ ዋንጫ ካጣ በኃላ የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ለፍፃሜ መብቃት አልቻሉም ነበር፡፡

በደቡብ አፍሪካዊው ፒትሶ ሞሴሜኔ የሚሰለጥነው ሰንዳውንስ የሪከርድ የደቡብ አፍሪካ ፕሪምየርሺፕ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዛማሌክ እና የሰንዳውንስ የመልስ ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት ይደረጋል፡፡

 

የሰንዳውንስን ሶስት ግቦች ለመመልከት ይህንን ሊንክ ይከተሉ https://www.youtube.com/watch?v=JnbmXPybk6c

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *