የቶታል አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ይፋ ሆኗል

ጋቦን በጥር 2017 ለምታስተናግደው የቶታል አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ዕረቡ ምሽት ሊበርቪል በተደረገ ስነ-ስርዓት ይፋ ሆኗል፡፡ 16 ሃገራት በአራት ምድብ የተደለደሉ ሲሆን የዕጣ ማውጣቱን ስነ-ስርዓት ማድረግ የቻሉት የቀድሞ የሴኔጋል ኮከቡ ካሊሉ ፋዲጋ፣ የጋናው አቡዱልከሪም ራዛክ እና የቀድሞው የጋቦን ኢንተርናሽናል ፍራንሶአ አሚጋሴ ናቸው፡፡
አዘጋጇ ጋቦን በምድብ አንድ በ2013 የፍፃሜ ተፋላሚ ከነበረችው ቡርኪናፋሶ፣ ከአራት ግዜ ሻምፒዮኗ ካሜሮን እና ለመጀመሪያ ግዜ በአህጉሪቱ ታላቅ ውድድር መሳተፍ ከቻለችው ጊኒ ቢሳው ጋር ተደልድላለች፡፡ በምድብ ሁለት የሰሜን አፍሪካ ሃያሎቹ አልጄሪያ እና ቱኒዚያ ከሴኔጋል እና ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ወደ ተመለሰችው ዚምባቡዌ ጋር ተደልድለዋል፡፡ የ2015 የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ኮትዲቯር በምድብ ሶስት ከዲ.ሪ ኮንጎ፣ ሞሮኮ እና ቶጎ ጋር ስትደለደል ብቸኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ዩጋንዳ ከጋና፣ ከሰባት ግዜ ሻምፒዮኗ ግብፅ እና ማሊ ጋር መድልደል ችለዋል፡፡ በ2015 ኮትዲቯር እንዲሁም በ2012 ዛምቢያን ለሻምፒዮንነት ያበቃው ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ ሞሮኮ የሚመራ ይሆናል፡፡ በ2018 ሩሲያ የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ በአንድ ምድብ የተደለደሉት ጋና፣ ግብፅ እና ዩጋንዳ በአፍሪካ ዋንጫው በተመሳሳይ አንድ ምድብ ውስጥ ተደልድለዋል፡፡
ጋቦን ውድድሩን ለማስተናገድ አራት ከተሞች መርጣለች፡፡ ዋና ከተማዋ ሊበርቪል፣ ፍራንስቪል፣ ኦየም እና ፖርት ጀንቲል ጨዋታዎቹን የሚያስተናግዱ ይሆናል፡፡ ካፍ ባወጣው መረጃ ከሆነ በምድብ አንድ የሚገኙ ሃገራት ሊበርቪል ላይ የሚቀመጡ ሲሆን በስታደ ለአሚታይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ የምድብ ሁለት ፍራንስቪልን መቆያቸው አድርገዋ በስታደ ፍራንስቪል የሚጫወቱ ይሆናል፡፡ የምድብ ሶስት ሃገራት በኦየም መቆያቸውን አድርገው ጨዋታቸውን በስታደ ደ ኦየም የሚያደርጉ ሲሆን የምድብ አራት ሃገራት በፖርት ጀንቲል ተቀምጠው በስታደ ደ ፖርት ጀንቲል የሚጫወቱ ይሆናል፡፡ የ2015 የአፍሪካ ዋንጫ በኢኳቷሪያል ጊኒ አስተናጋጅነት ሲካሄድ ኮትዲቯር ጋናን በመለያ ምት በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት መሆኗ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *