የከፍተኛ ሊግ እጣ ማውጣት ስነ ስርአት ተካሂዷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን የእጣ ማውጣት ስነ ስርአት ፣ የአምናው ውድድር ሪፖርት እና ውይይት ዛሬ በካፒታል ሆቴል ተካሂዷል፡፡ ረፋድ 3:30 የተጀመረው ፕሮግራም እስከ ምሽት 1:00 የዘለቀ ሲሆን በውይይቱ የተወሰኑ ውሳኔዎች ክና ዋና ዋና ጉዳዮች እንዲሁም የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

 

የውድድሩ ፎርማት ባለበት ይቀጥላል

 

በካፒታል ሆቴሉ ውይይት ከፍተኛውን ቦታ የያዘው የውድድሩ ፎርማት ጉዳይ ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ 4 አይነት ፎርማቶች የቀረቡ ሲሆን አምና የነበረው የ2 ምድብ ውድድር እንዲቀጥል ከውሳኔ ተደርሷል፡፡ በ3 ምድቦች ማካሄድ ፣ በ2 ምድቦች ተከፍሎ ነገር ግን የመልክአ ምድራዊ አቀማመጣቸውን ያላመማከለ ድልድል እንዲሁም የየክልሎቹን ክለቦች ያመጣጠነ ድልድል በውይይቱ ላይ የተነሱ ሌሎች አማራጮች ነበሩ፡፡

 

3 ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያድጋሉ

 

በከፍተኛ ሊጉ ምድባቸውን በ1ኝነት የሚያጠናቅቁ 2 ክለቦች በቀጥታ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያልፉ ምድባቸውን በ2ኝነት የሚያጠናቅቁ ክለቦች በሚያደርጉት የመለያ ጨዋታ 3ኛው ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያድጋል፡፡

ከየምድባቸው 14ኛ ፣ 15ኛ እና 16ኛ የሚወጡ 6 ክለቦች ክለቦች ወደ ብሄራዊ ሊግ የሚወርዱ ይሆናል፡፡

 

ሙገር ሲሚንቶን የሚተካው ክለብ አልታወቀም

 

በከፍተኛ ሊጉ ከሚወዳደሩ ክለቦች መካከል ሙገር ሲሚንቶ እና ዳሽን ቢራ ክለቦቻቸውን አፍርሰዋል፡፡ በዳሸን ቢራ ምትክ በምድብ ሀ 15ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው አክሱም ከተማ ሲተካ ሙገር ሲሚንቶ ግን በእጣው ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ የምድብ ሀ በ15 ክለቦች ይቀጥል አልያም የሙገር ተተኪ ማን ይሁን የሚለው ምላሽ ሳይሰጠው ታልፏል፡፡

 

 

የሚጀመርበት ቀን በ15 ቀናት ተራዝሟል

 

የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሚጀመርበት ቀን በ2 ሳምንታት ተራዝሞ ህዳር 17 እንዲጀመር ተወስኗል፡፡ ክለቦች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት በተሰጠው አብላጫ ድምጽ ነው ውድድሩ እንዲራዘም የተደረገው፡፡ የውድድሩ መራዘምን ተከትሎ ሰኔ 7 ይጠናቀቃል የተባለው ውድድር ወደ ሰኔ 21 የሚገፋው ይሆናል፡፡

 

የከፍተኛ ሊግ ክለቦች በጥሎ ማለፍ ላይ መሳተፍ ይችላሉ

ከ2002 በኋላ በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል ብቻ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድር በዚህ አመት የከፍተኛ ሊግ ክለቦችንም እንዲያሳትፍ ተደርጓል፡፡ በዛሬው ውይይት ላይ በተነሳው ሀሳብ መሰረት የከፍተኛ ሊግ ክለቦች በሙሉ ይሳተፉ ወይም አይሳተፉ በሚለው ላይ ድምጽ ተሰጥቶ አለመሳተፍ የሚለው ሀሳብ በ1 ብቻ ድምጽ ልዩንት ተቀባይነት ቢያገኝም በመጨረሻ በተሰጠው ሀሳብ በውድድሩ ላይ መሳተፍ የሚፈልግ እንዲወዳደር ፣ የማይፈልግ ያለመሳተፍ መብቱ እንደሚከበርለት ከውሳኔ ተደርሶ በቀጣዩ አመት ግን ሁሉም የከፍተኛ ሊግ ክለቦች የመሳተፍ ግዴታ እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡

 

የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታዎች

ምድብ ሀ

ቅዳሜ ህዳር 17 ቀን 2009

ሙገር ሲሚንቶ ከ አማራ ውሃ ስራ (አበበ ቢቂላ)

እሁድ ህዳር 18 ቀን 2009

ባህርዳር ከተማ ከ አክሱም ከተማ (ባህርዳር)

ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ከ ለገጣፎ ከተማ (አበበ ቢቂላ)

ወሎ ኮምቦልቻ ከ አራዳ ክ/ከተማ (ኮምቦልቻ)

ኢትዮጵያ መድን ከ ሽረ እንዳስላሴ (መድን ሜዳ)

ቡራዩ ከተማ ከ አዲስ አበባ ፖሊስ (ቡራዩ)

መቀለ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ (መቀለ)

ሱሉልታ ከተማ ከ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ (ሱሉልታ)

 

ምድብ ለ

እሁድ ህዳር 18 ቀን 2009

ጅማ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ (ጅማ)

ነገሌ ቦረና ከ ወልቂጤ ከተማ (ነገሌ ቦረና)

ናሽናል ሴሜንት ከ አርሲ ነገሌ (ድሬዳዋ)

ጌድዮ ዲላ ከ ድሬዳዋ ፖሊስ (ዲላ)

ጂንካ ከተማ ከ ስልጤ ወራቤ (ጂንካ)

ፌዴራል ፖሊስ ከ ሻሸመኔ ከተማ (አበበ ቢቂላ)

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ካፋ ቡና (ሆሳዕና)

ነቀምት ከተማ ከ ሀላባ ከተማ (ነቀምት)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *