የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 አመት በታች ሊጎች እጣ ማውጣት ስነስርአት በካፒታል ሆቴል እና ስፓ በጋራ ተካሂዷል፡፡ በስነስርአቱ የ2008 የ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ሪፖርት እና የዘንድሮው የውድድር ዘመን ደንብ የቀረበ ሲሆን ከድንገተኛ ጉዳቶች ጋር የተያያዘ ማብራርያ እና የእድሜ ጉዳይ ላይ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላም የእጣ ማውጣት ስነ ስርአቱ ተካሂዷል፡፡
በእረፍት ቀናት ይካሄዳል
ውድድሩ የወጣቶች እንደመሆኑ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ እንዲደረጉ በተነሳው ሀሳብ ላይ ውይይት ተካሂዶ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
የውድድሩ መጀመርያ ቀን ተለውጧል
የ17 አመት በታች እና 20 አመት በታች ሊጎች የመጀመርያ ቀናት ላይ የቀን ለውጥ ተደርጎ ሁለቱም ሊጎች ህዳር 27 እንዲጀምሩ ተወስኗል፡፡
የማጠቃለያ ውድድር አይኖርም
ፌዴሬሽኑ በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ እንዳደረገው ሁሉ በ2 ምድብ የተከፈለው የ17 አመት በታች ሊግ የማጠቃለያ ውድድሩ እንዲቀር አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት የምድቦቹ አሸናፊዎች ለሊጉ ቻምፒዮንነት ሲጫወቱ ከምድባቸው 2ኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች ለደረጃ ይጫወታሉ፡፡
የጥሎ ማለፉ ጉዳይ አለየለትም
ከሊጉ ውድድር በተጨማሪ እንዲካሄድ ሀሳብ በቀረበበት የጥሎ ማለፍ ውድድር ላይ ክለቦች የተለያየ ሀሳብ በማንፀባረቃቸው መካሄድ አለመካሄዱ ወደፊት ይገለጻል ተብሏል፡፡
የእድሜ ማጭበርበርን መከላከል. . .
ፌዴሬሽኑ የእድሜ ማጭበርበርን ለመቆጣጠር የተለያዩ አሰራሮችን እየተከተለ እንደሆነ የህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነስረዲን ገልፀዋል፡፡ ልዩ መለያ ኮድ ያለው መታወቂያ ማዘጋጀት እና ፌዴሬሽኑ በመረጣቸው የህክምና መስጫ ተቋማት ብቻ የMRI ምርመራ ማድረግ ከመቆጣጠርያ መንገዶቹ መካከል ናቸው ተብሏል፡፡
ከ20 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ
ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄደው የ20 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ 12 ክለቦችን የሚያሳትፍ ሲሆን በዞን ሳይከፋፈል ወጥ በሆነ ፎርማት ይካሄዳል፡፡
በወጣው እጣ መሰረት የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ድሬዳዋ)
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዋሳ ከተማ (አአ)
አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ (አዳማ)
መከላከያ ከ ደደቢት (አአ)
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ መድን (አአ)
ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮጵያ ቡና (ሶዶ)
ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ
17 ክለቦችን የሚያሳትፈው የዘንድሮው ከ17 አመት ፕሪሚየር ሊግ እንደዚህ ቀደሙ በሁለት ምድብ ቢከፈልም የመልክአ ምድራዊ አቀማመጣቸውን ያማከለ ድልድል ቀርቶ በእጣ እንዲደለደለ ተደርጓል፡፡
የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታዎች የሚከተሉች ናቸው
ምድብ ሀ
ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ፎም (አአ)
መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (አአ)
ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (ሀዋሳ)
ኢትዮጵያ መድን ከ አፍሮ ፅዮን ኮ. (አአ)
ምድብ ለ
ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ (አአ)
ኒያላ ከ አዳማ ከተማ (አአ)
ተ/ብርሃን አምባዬ ከ ሲዳማ ቡና (አአ)
ደደቢት ከ አዲስ አበባ ከተማ (አአ)
አራፊ ቡድን – ቅዱስ ጊዮርጊስ