የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች ልምምድ አቋረጡ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው አዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች ክለቡ እንዲያሟላላቸው የሚፈልጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በማስቀመጥ ከዛሬ ጀምሮ ልምምዳቸውን አቋርጠዋል፡፡

ተጫዋቾቹ ልምምድ ለማቋረጥ ያበቃቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሶስት ሲሆኑ ከመስከረም ወር ጀምሮ ያልተከፈላቸው ደሞዝ እንዲከፈላቸው ፣ የትጥቅ አቅርቦት እንዲሟላ እና ልምምዳቸውን የሚያከናውኑበት የአበበ ቢቂላ ስታድየም ለጤንነታቸው አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ ተለዋጭ የልምምድ ሜዳ እንዲዘጋጅላቸው በመጠየቅ ነው፡፡ ክለቡ ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ካልሰጠ ልምምድ ባለመስራት እንደሚቀጥሉ ታውቋል፡፡

ክለቡ እስሁን ደሞዝ ያልከፈለበትን ምክንያት ለማጣራት ባደረግነው ጥረት ባገኘነው መረጃ መሰረት ለሁሉም ተጫዋች የሚከፈለው ደሞዝ ለቦርድ ቀርቦ ማስተካከያ እንዲደረግበት በመወሰኑ ክፍያው እስካሁን ዘግይቷል፡፡ በመጪዎቹ ቀናትም ለተጫዋቾች የሚከፈለው ደሞዝ እንደሚለቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

OLYMPUS DIGITAL CAMERA
OLYMPUS DIGITAL CAMERA

በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ክለብ የሴቶች ቡድን እጣ ፈንታ አስካሁን አልታወቀም፡፡ ዘንድሮ የተቋቋመውና አስራት አባተን አሰልጣኝ አድርጎ በመሾም በርካታ ተጫዋቾችን ያሰባሰበው የሴቶች ቡድኑ መፍረሱን ከሳምንት በፊት ያስታወቀ ሲሆን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚር ሊግ ላይ እንደማይሳተፍ በደብዳቤ አሳውቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ እንደሚሳተፉ አስታውቀው በምድብ ድልድል ውስጥ ከተካተቱ በኋላ ሃሳባቸውን መቀየር እንደማይችሉ በመግለጽ ቡድኑ ከፈረሰ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡ ይህን ተከትሎም በቡድኑ መፍረስ አለመፍረስ ዙርያ ቦርዱ ለሁለት መከፈሉና ውሳኔ ለማሳለፍ መቸገሩም ተሰምቷል፡፡  የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሊጀመር 2 ሳምንት ብቻ በቀረበት በዚህ ወቅት ክለቡ እስካሁን ዝግጅት አልጀመረም፡፡

Leave a Reply