የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ኮትዲቯሯዊው አጥቂ ኢብራሂም ፎፋኖ የ11ኛው አዲስ አበባ ዋንጫ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተሸልሟል፡፡ በኤሌክትሪክ በፍጥነት የተላመደው ፎፋኖ ተከላካዮችን የመረበሽ እንዲሁም ፍጥነቱ ኤሌክትሪክን ለከተማው ዋንጫ ቻምፒዮንነት አብቅቶታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሶስት ግቦችን (ሁለት በፍፃሜው) ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ከብሩንዳዊው ዲዲዮ ካቩምባጉ እና ወደ ድንቅ አቋሙ እየተመለሰ ሚገኘው ዳዊት እስጢፋኖስ ጋር ጥሩ ቅንጅትን መፍጠር ችሏል፡፡
ፎፋኖ በፍፃሜው ቅዱስ ጊዮርጊስን 2-0 በማሸነፋቸው የተሰማውን ደስታ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡ “ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ቀላይ ጨዋታ አልነበረም ለማሸነፍ ጠንካራ ሆነን መቅረብ ነበረብን፡፡ ነገር ግን ማሸነፍ ችለናል በዚህም ውጤቱ ጥሩ ነው፡፡” ፎፋኖ ሲቀጥል በፍፃሜው ጨዋታ ሁለት ግብ ማስቆጠሩ ይበልጥ ደስተኛ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ “በፍፃሜ ጨዋታ ሁለት ግብ ማስቆጠር መቻሌ ይበልጥ ደስተኛ አድርጎኛል፡፡ በግቦቼ ቡድኔ ዋንጫ ማንሳት መቻሉ ለኔ ትልቅ ደስታ ነው፡፡”
ባለፉት ጥቂት አመታት በውጤት ቀውስ ምክንያት ላለመውረድ ሲጫወት የነበረው ኤሌክትሪክ በቀጣዩ ሳምንት በሚጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተሻለ ውጤት እንደሚያሰመዘግብ ፎፋኖ ይናገራል፡፡ “ኤሌክትሪክ በአዲሱ የውድድር ዓመት በተሻለ መልኩ የቀረበ ይመስለኛል፡፡ ክለቡ ትልቅ ክለብ ስለሆነ በያዝነው የውድድር ዓመት ጥሩ ውጤት ያስለመዘግባል፡፡ በባለፈው ዓመት ክለቡ ጥሩ ደረጃ ላይ አይገኝም ነበር አሁን ግን አሰልጣኛችን ጥሩ ስራ በመስራቱ ክለቡ እየተሻሻለ ይገኛል፡፡ ጥሩ የውድድር ዓመት እንደምናሳልፍ እገምታለው፡፡” ሲል ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡