የሶከር ኢትዮጵያ የ2008 የዓመቱ የእግርኳስ ሰዎች ሽልማታቸውን ተቀበሉ

የ2008 የሶከር ኢትዮጵያ የዓመቱ የእግርኳስ ሰዎች ተብለው በአንባቢያን እና በድህረ-ገፁ አዘጋጆች የተመረጡት ጌታነህ ከበደ እና ሎዛ አበራ ማክሰኞ ዕለት የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ደደቢት የፊት መስመር ተሰላፊው ጌታነህ በወንዶች ዘርፍ ከተሰጠው ድምፅ 68% በማግኘት የዓመቱ ምርጥ የእግርኳስ ሰው ሆኗል፡፡ ሎዛ አበራ በበኩሏ በሴቶች እግርኳስ ዘርፍ ከተሰጠው ድምፅ 86% በማግኘት ማሸነፍ ችሏለች፡፡

ለሁለተኛ ግዜ በተደረገው የሶከር ኢትዮጵያ የዓመቱ የእግርኳስ ሽልማት ጌታነህ ከበደ ለመጀመሪያ ግዜ በወንዶች እግርኳስ ሰፊ ድምፅ በማግኘት ነው ማሸነፍ የቻለው፡፡ በውድድር ዓመቱ ለዋልያዎቹ ተሰልፎ በዓለም ዋንጫ እንዲሁም በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻለው ጌታነህ ጋቦን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በተደረጉ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ከመረብ ማዋሃድ ችሏል፡፡ በተለይ ኋያሏ አልጄሪያ ላይ ሶስት ግቦችን በሁለት ጨዋታዎች ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡ ወደ ደበብ አፍሪካ ናሽናል ፈርስት ዲቪዢን ለወረደው የፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ ሁለት ግቦች ሲያስቆጥር አራት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡ የዋሊያዎቹን የፊት መስመር የመምራት ሃላፊነት በውድድር ዓመቱ ለብቻው የተሸከመው ጌታነህ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አጥቂው ሌሶቶ ላይ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የአጨራረስ ብቃቱን ያስመሰከሩ ነበሩ፡፡

img_2016

ጌታነህ ሽልማቱን ከሶከር ኢትዮጵያ ኤዲተር ዳንኤል መስፍን እጅ ከተቀበለ በኃላ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡ “በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በዓመቱ ባሳየሁት እንቅስቃሴ የዓመቱ ምርጥ የእግርኳስ ሰው ተብዬ በመመረጤ ደስ ብሎኛል፡፡ የመጀመሪው የወንድ ተሸላሚ መሆኔም በጣም አስደስቶኛል፡፡ ሁሌም የመጀመሪያ ስትሆን ደስታው የተለየ ነው የሚሆነው፡፡ በሃገር ውስጥ እግርኳስ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጋ በምትሰራው ሶከር ኢትዮጵያ መሸለሜ ደስ ብሎኛል፡፡”

ጌታነህ ሲቀጥል በውድድር ዓመቱ የተሻለ መንቀሳቀሱ ቢያስደስተውም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ አለማለፏ የፈጠረበትን ቁጭት ከመግለፅ አልተቆጠበም፡፡ “ጥሩ የሆነ ስኬታማ ዓመት አሳልፊያለው ነገር ግን ትንሽ ቁጭት ነበረኝ፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ ዓይነት ነገር ስታመጣ ጥሩ የሚሆነው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ብቻ ነበር፡፡ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ብናልፍ ይህ ስኬቴ እጥፍ ድርብ ይሆን ነበር፡፡ ያም ሆኖ ያሳየሁት ብቃት እና ዓመቱ በጣም ጥሩ ነበር፡፡”

img_2021

ወደ ቀድሞ ክለቡ ደደቢት ዳግም የተመለሰው ጌታነህ ሽልማቱ በያዝነው የውድድር ዓመት የተሻለ እንዲንቀሳቀስ እንደሚያደርገው ይናገራል፡፡ “ሽልማቶች ሁልግዜም የተሻለ እንድትሰራ ነው የሚያደርጉት፡፡ ጠንክሬ ሰርቼ በዘንድሮው ዓመት ይህንን ሽልማት ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ ሽልማቶች እወስዳለው ብለህ ታስባለህ፡፡”

ሎዛ አበራ በሴቶች እግርኳስ ዘርፍ የአመቱ የሴት እግርኳስ ዘርፍ ያሸነፈችው በሰፊ ድምፅ ነበር፡፡ የሉሲዎቹ እና የደደቢት አጥቂ የሆነችው ሎዛ በተሰለፈችባቸው ጨዋታዎች ግብ አዳኝነቷን አስመስክራለች፡፡ በዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ስድስት ግቦች ከመረብ ስታሳርፍ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 57 ግቦች ከመረብ አዋህዳለች፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አልጄሪያ ላይ አንድ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡ በሴካፋ ሴቶች ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ሶስተኛ ደረጃ ይዛ እንድታተናቅቅ አራት ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ሚናን ተጫውታለች፡፡ የሎዛ ግቦች ክለቧን ደደቢት ለሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊነት ለማብቃት የነበራቸው ስፍራ ትልቅ ነበር፡፡

img_1961

ሎዛ ሽልሟቷን ከሶከር ኢትዮጵያ ኤክስኪቲቭ ኤዲተር ኦምና ታደለ ከተቀበለች በኃላ የመረጧትን አንባቢያን አመስግናለች፡፡ “በመጀመሪያ ለዚህ ሽልማት ያበቃኝን እግዚአብሄርን እጅግ አድርጌ አመስግናለው፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ሁሉንም የመረጡኝንም የሶከር ኢትዮጵያ አዘጋጆችንም ጨምሮ በጣም አድረጌ ለማመስገን እወዳለው፡፡ የመረጡኝን፣ የደገፉኝን ሁሉንም ባአጠቃላይ አመሰግናለው፡፡ ይመጥናታል ብለው ለዚህ ሽልማት ስለረዱኝ በጣም አድርጌ አመሰግናለው፡፡”

ሎዛ በ2009 የውድድር ዓመት የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሽልማቱን እንደሚያነሳሳት ተናገራላች፡፡ “ይህ የመጀመሪያ ሽልማቴ ነው፡፡ በቀጣይም እንደዚሁ ለመሸለም ነው የምፈልገው፡፡ ከዚህ የበለጠ እንድሰራ እና የተሻለ እንቅስቃሴ እንዳሳይ እንዲሁም ጠንካራ እንድሆን ይረዳኛል፡፡ ከባለፈው ዓመት ከሰራኃቸው ስራዎች በተሻለ ውጤታማነቴን ማስቀጠል ነው የምፈልገው፡፡”

img_1952

በ2007 ድሬዳዋ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲቀላቀል ያስቻለችው አሰልጣኝ መሰረት ማኔ የውድድሩ አሸናፊ መሆኗ የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply