ፋሲል ከተማን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ላሳደጉ አባላት ሽልማት ተበረከተላቸው

ባለፈው የውድድር ዘመን የከፍተኛ ሊጉን በቻምፒዮንነት አጠናቆ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ላደገው ፋሲል ከተማ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ትላናት 08:00 ላይ በላንድ ማርክ ሆቴል የዕውቅና እና የሽልማት ስነ ስርአት ተደረጎለታል፡፡

የሽልማት መጠኑ እንደየስራ ድርሻቸው እና ባበረከቱት አስተዋጽኦ መጠን የተከፋፈለ ሲሆን 130,000 ብር የተበረከተላቸው ዋና አሰልጣኙ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ከፍተናውን ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ለረዳት አሰልጣኙ 90,000 ፣ ለቡድን መሪ 100,000 ፣ ለህክምና ባለሙያ 60,000 ፣ ለተጨዋቾች በተጫወቱት ብዛት ተሰልቶ የመጀመሪያ ደረጃዎች  100,000 ፣ ለሁለተኛ ደረጃ 90,000 ፣ ለሦስተኛ ደረጃ 85,000 ሽልማት ተበርክቶላችዋል፡፡ ይህን ሽልማት አጠቃላይ ወጪ የሸፈነውም የጎንደር ከተማ አስተዳደር እንደሆነ ተገልጧል፡፡

በሽልማት ስነ ስርአት ወቅት የፈረሰው ዳሽን ቢራ አምና ይገለገልበት የነበረውን ዘመናዊ የተጨዋቾች መመላለሻ አውቶብስ ለፋሲል ከተማ የለገሰ ሲሆን ወደፊትም ክለቡን በማንኛውም ረገድ ለመደገፍ አስፈላጊውን ነገር እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል፡፡ ፋሲል ከተማ በከፍተኛ ሊግ በነበረው ተሳትፎ የገንዘብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ ያደርግለት የነበረው የጎንደር ዮንቨርስቲም ቡድኑ በፕሪሚየር ሊግ በሚያደርገው ቆይታው እንደ ወትሮው ሁሉ ድጋፉ እንደማይለየው አስታውቋል ።

በተያያዘ ዜና ለ2009 የውድድር ዘመን የሚጫወትበት አዲስ ማሊያ ከውጭ እንዳስመጣ የታወቀ ሲሆን እና በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት የፋሲል ከተማ የሜዳ ጨዋታዎች በተለዋጭ ሜዳዎች ሊደረግ እንደሚችል ቢገመትም ክለቡ ሁሉንም የሜዳው ጨዋታዎች በጎንደር ፋሲለደስ ስታድየም እንደሚያከናውን ለማወቅ ችለናል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዳሜ እና እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሲጀመር ፋሲል ከተማ ከ8 አመታት በኋላ የመጀመርያ የሆነውን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በመጪው እሁድ 09፡00 ይርጋለም ስታድየም ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ያደርጋል፡፡

 

 

Leave a Reply