ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን ለከተማው ዋንጫ ፍፃሜ ደረሱ

በ8 ሰአት የአምናው የፍፃሜ ተፋላሚ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ መድን ተሸንፎ ለተከታታይ አመታት ለፍፃሜ የመቅረብ ህልም ተጨናግፏል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር በተደረገበት በዚህ ጨዋታ ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ብቸኛዋ ግብ ተቆጥራለች፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች እና የአሰላለፍ ለውጥ ሲያደርጉ ንግድ ባንክ የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር መድንም ውጤቱን ለማስጠበቅ ትግል አድርገዋል፡፡ በጨዋታው መጠናቀቅያ የመጨረሻ ደቂቃ ናይጄርያዊው ፊሊፕ ዳውዚ ያገኘውን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይጠቀምበት መቅረቱ ለንግድ ባንክ በአስቆጪነቷ ትጠቀሳለች፡፡

የአስራት ኃይሌው መድን በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለፍፃሜ ሲደርስ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡

በ10 ሰአት የተደረገውና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የሁለቱ ባላንጣ ክለቦች ፍልሚያ የተጠበቀውን ፉክክር ሳያሳይ በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት ተጠናቋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመርያውን ግብ ያስቆጠሩት በ13ኛው ደቂቃ በፍፁም ገብረማርያም አማካኝነት ነው፡፡ ፍፁም ተፈሪ በቡና የግብ ክልል በተፈፀመበት ጥፋት የተገኘው የፍፁም ቅጣት ምት ውዝግብን ፈጥራ የደጋፊ ተቃውሞን አስከትላለች፡፡ ከፍፁም ቅጣት ምቷ መቆጠር 2 ደቂቃ በኃላ ሳሙኤል ሳኑሚ ሁለተኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ከሁለቱ ግቦች መቆጠር በኋላ ቀሪውን የመጀመርያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና የበላይነት ቢወስድም ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ሚዛኑ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያጋድል ሳሙኤል ሳኑሚ በድንቅ ቅጣት ምት እንዲሁም ፍፁም ገብረማርያም የጨዋታው ሁለተኛ ግቦቻቸውን አስቆጠረዋል፡፡

ከረጅም ጊዜ ጉዳት በቅርቡ ወደ ሜዳ የተመለሰው የቀድሞው የሙገር አጥቂ ፍፁም በሲቲ ካፑ ያስቆጠራቸውን ግቦች ቁጥር 5 አድርሶ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ