8ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ ዛሬ የሚደረጉት ሁለት ወሳኝ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች የፍፃሜ ተፋላሚዎችን ይለያል፡፡ ምድብ አንድን በ7 ነጥቦች 1ኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምድብ ሁለትን ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ መድንን በ9፡00 በአዲስ አበባ ስታዲየም ይገጥማል፡፡ የአምናው የፍፃሜ ተፋላሚ ንግድ ባንክ በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም እየተመራ ልዩ የውድድር ዘመን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ አሰልጣኙ የስኳድ ስፋታቸውን በሲቲ ካፑ በአግባቡ የተጠቀሙበት ሲሆን ይህን ጨዋታ አሸንፎ ለፍፃሜ መድረስ ላማረው የሊግ ጉዟቸው ተጨማሪ መነሳሻ ይሆንላቸዋል፡፡
የአስራት ኃይሌ ኢትዮጵያ መድንም በፕሪሚየር ሊጉ ባሳየው ዘገምተኛ መሻሻል በመቀጠል በከተማው ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍፃሜ መግባት ችሏል፡፡ በሊጉ ወራጅ ቀጠና እየዳከረ ያለው ኢትዮጵያ መድን እንደ ንግድ ባንክ ሁሉ ጨዋታውን እንደ ትልቅ መነሳሻ ይጠቀሙበታል፡፡
ሁለቱ ክለቦች ፕሪሚየር ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በነበረው የመጨረሻ ሳምንት ተገናኝተው ሃምራዊዎቹ በኤልያስ ማሞ ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
ምድብ ሁለትን በበላይነት ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ * ‹‹ አውዳመት ›› የምድብ 1 ሁለተኛው ኢትዮጵያ ቡናን ይገጥማል፡፡ ውድድሩ በተመልካች ድርቅ እንደመመታቱና ብዙም የሚድያ ትኩረት ባለመሳቡ ይህ ጨዋታ የተመልካቹን እና የመገናኛ ብዙሃንን ስሜት ያነቃቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአመዛኙ ወጣቶችን እና ከጉዳት ለረጅም ጊዜያት ርቀው በተመለሱ ተጫዋቾች ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስና በተመሳሳይ ወጣቶችን የተጠቀመው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ፍልምያ ምንግዜም የውድድር ደረጃ እና የሚጠቀሙባቸው ተጫዋቾች ጥራት ተፅእኖ የማይፈጥርበት የሃገሪቱ ትልቅ ፍልሚያ ነው፡፡
ሁለቱ ታላላቆች በሊጉ 6ኛ ሳምንት ላይ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ በኡመድ ኡኩሪ እና አይዛክ ኢሴንዴ ግቦች 2-0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
* ‹‹ አውዳመት ›› የሚለውን ስያሜ ሶከር ኢትዮጵያ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ የምትጠቀምበት ሲሆን በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወቅት በከተማ ውስጥ በሚፈጠረው አስደናቂ ድባብ መነሻነት የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሚቾ “ the public holiday “ የሚል መጠርያ ሰጥተውታል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ቃሉ ለፍልሚያው ተስማሚ መጠርያ ሆኖ ስላገኘችው በአማርኛ ቃል ፍቺው ትጠቀምበታለች፡፡
{jcomments on}