ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ ከተማ : ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ


ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም

ቀን – ቅዳሜ ህዳር 3 ቀን 2009

ሰአት – 10፡00

ስርጭት – ቀጥታ የፅሁፍ ስርጭት በሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገጽ


የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊጉ አዲሱ የውድድር ዘመን ነገ ሲጀመር የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ ሁለቱም ክለቦች ከቅድመ ውድድር ጨዋታዎች የፍጻሜ ሽንፈት በኋላ የውድድር ዘመኑን በድል ለመክፈት 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይፋለማሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ፍጻሜ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ተሸንፎ ዋንጫውን ያጣው ቀዱስ ጊዮርጊስ ከአምናው እምብዛም ለውጥ ያላሳየ ቡድን የያዘ ይመስላል፡፡ በዝውውር መስኮቱ የተቀዛቀዘ እንቀስቃሴ ማሳየቱ እና ከውጭ ያስመጣቸው ተጫዋቾች በደጋፊዎች በጥርጣሬ መታየታቸው እንዲሁም የወሳኝ ተጫዋቾቹን አገልግሎት አለማግኘቱ በጨዋታው እንዲፈተን ሊያደርገው ይችላል፡፡

እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ በደቡብ ካሰቴል ዋንጫ ፍፃሜ በሲዳማ ቡና ተሸንፎ ዋንጫውን ያጣው አርባምንጭ ከተማ ካለፉት አመታት በተሻለ የተጫዋቾች ዝውውር ማድረግ ችሏል፡፡ ወነድሜነህ ዘሪሁን ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና ወንድወሰን ሚልኪያስ አምና በሊጉ ተቸግሮ የነበረው አርባምንጭ ከተማን ያሻሽሉታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አርባምንጭ መጥፎ ያልሆነ የተከላካይ መስመር እና ልዩነት ሊፈጥር የሚችል የአማካይ ክፍል ቢኖረውም የፊት መስመሩ የቡድኑ ደካማ ክፍል ነው፡፡


img_1895


ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ዘሪሁን ታደለ

ፍሬዘር ካሳ – አስቻለው ታመነ – ደጉ ደበበ – መሀሪ መና

ምንተስኖት አዳነ – ምንያህል ተሾመ

በኃይሉ አሰፋ – አዳነ ግርማ – አቡበከር ሳኒ

ሳላዲን ሰኢድ

አርባምንጭ ከተማ (4-5-1)

አንተነህ መሳ

ወርቅይታደል አበበ – በረከት ቦጋለ – ተመስገን ካስትሮ – ተካልኝ ደጀኔ

እንዳለ ከበደ – ምንተስኖት አበራ – አማኑኤል ጎበና (አምበል) – ወንድሜነህ ዘሪሁን – ታደለ መንገሻ

አመለ ሚልኪያስ


ቁልፍ ነጥቦች

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች

የፈረሰኞቹ ደጋፊዎች የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ድምቀት ነበሩ፡፡ አዳዲስ ዝማሬዎችን በመፍጠር ቡድናቸውን ከማበረታታቸው በተጨማሪ ከዚህ ቀደም እንደማብሸቂያ ይሰነዘሩባቸው የነበሩ ቃላትን ለቡድናቸው ማበረታቻነት ሲጠቀሙ ተስተውለዋል፡፡ የነገው የሊጉ መክፈቻንም ያደምቁታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአርባምንጭ አማካይ ክፍል

የአርባምንጭ ከተማ የአማካይ ክፍል አወቃቀር የተሟላ ይመስላል፡፡ ጠንካራ የመከላከል ብቃት ያለው አማኑኤል ፣ ታታሪው ምንተስኖት ፣ ቀጥተኛው እንዳለ ፣ ጨዋታ አቀናባሪው ወንድሜነህ እና ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ለአጥቂዎች የሚያቀርበው ታደለ መንገሻን የያዘው የአርባምንጭ ከተማ የአማካይ ክፍል በወረቀት ላይ ሲታይ በሊጉ ካሉት የተሟላ የአማካይ ክፍል ይመስላል፡፡ አሰልጣኝ ጳውሎስ ተስፋዬም ከአማካይ ክፍሉ የመጨረሻውን ብቃት የማውጣት ሃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡

ሮበርት ኦዶንካራ እና አይዛክ ኢዜንዴ

ዩጋንዳ በዛምቢያ በተሸነፈችበት የወዳጅቸነት ጨዋታ ሁለቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ተሰልፈው ተጫውተዋል፡፡ ነገ በአለም ዋንጫ ማጣርያ ኮንጎ ዲ.ሪ.ን በሚገጥመው ቡድን ውስጥም ተካተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለይም የሮበርት ኦዶንካራን ግልጋሎት አለማግኘቱ ትልቅ ክፍተት ይፈጥርበታል፡፡ በሲቲ ካፑ ፍጻሜ ለሁለቱም ግቦች መቆጠር ምክንያት የነበረው ዘሪሁን ታደለ እና በሊግ ጨዋታዎች ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተሰልፎ የማያውቀው ፍሬው ጌትነት የዩጋንዳዊውን ክፍተት የመሙላት ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡

የጉዳት እና ቅጣት ዜናዎች

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በጉዳት ጨዋታው የሚያልፈው ተጫዋች የለም፡፡ ሆኖም በግል ጉዳይ ከአሰልጣኙ ፍቃድ የተሰጠው ተስፋዬ አለባቸው ልምምድ ያልሰራ ሲሆን በነገው ጨዋታ ላይሰለፍ ይችላል፡፡ ከባለቤቱ ሁለተኛ ልጅ የተበረከተለት ደጉ ደበበ ትላንት ልምምድ ባይሰራም ነገ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡
ጉዳት ላይ የነበሩት በኃይሉ አሰፋ ፣ ሳላዲን በርጊቾ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና አሉላ ግርማ ከጉዳት አገግመው ለጨዋታው ብቁ ሲሆኑ ከዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር ያሉት ሮበርት ኦዶንካራ ፣ ያስር ሙጌርዋ እና አይዛኬ ኢዜንዴ የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው ፡፡

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ወንድወሰን ሚልኪያስ እና ተሾመ ታደሰ በልምምድ ላይ በደረሰባቸው ጉዳት ወደ ከቡድኑ ጋር አዲስ አበባ ያልመጡ ሲሆን የእንዳለ ከበደ ከጉዳት አገግሞ መሰለፍ ለአርባምንጭ መልካም ዜና ነው፡፡

ጨዋታውን ማን ይመራዋል?

የነገውን የፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታ የ2007 የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ዳኛ ኢንተርናሽናል አርቢቴር ኃይለየሱስ ባዘዘው ይመራዋል::

የቅርብ ጊዜ ግንኙነቶች

ሁለቱ ክለቦች ባለፈው የውድድር ዘመን 3 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ አርባምንጭ ላይ ባደረጉት የመጀመርያ ዙር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ሲያሸንፍ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የ2ኛ ዙር ጨዋታ 1-1 ተለያይተዋል፡፡ አዳማ ላይ ባደረጉት ሊግ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 አሸንፏል፡፡


Leave a Reply