የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል በተካሄደው ጨዋታ ተጀምሯል፡፡ በነገው እለትም 7 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ፡፡ በዚህ ፅሁፍ የ6ቱን ጨዋታዎች በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

አዳማ ከተማ በክረምቱ ባደረገው እንቅስቃሴ ለፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮንነት ሁነኛ ተፎካካሪ ለመሆን ቆርጦ የተነሳ ይመስላል፡፡ በ2008 ወደ ፕሪሚር ሊግ የተመለሰው የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን በተከታታይ ሁለት አመታት 3ኛ በመውጣት ወጥ አቋም ያሳየ ሲሆን ዘንድሮ ደረጃቸው እና ወቅታዊ አቋማቸው ላቅ ያሉ ተጫዋቾችን በማሰባሰብ የውድድር ዘመኑን ይጀምራል፡፡

አዳማ ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ያሳየው ብቃት ቡድኑ ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚችል ያሳየ ነው፡፡ በአማራጮች የተሞላ ስብስብ ሲሆን ከአንጋፋቹ ታፈሰ ተስፋዬ እና ሱሌይማን መሃመድ ፣ በብቃታቸው ጫፍ ላይ የሚገኙት ሙጂብ ቃሲም እና ብሩቅ ቃልቦሬ ፣ በሊጉ እንደሚደምቁ የሚጠበቁት ወጣቶቹ ሱራፌል ዳኛቸው እና በረከት ደስታን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ስንመለከት ቡድኑ የተሟላ ስብስብ ይዟል ለማለት ያስደፍራል፡፡

አሰልጣኝ መሰረት ማኒን ተክተው የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ የሆኑት ዘላለም ሽፈራው በምስራቋ ከተማ በሒደት የሚሻሻሻል ቡድን እየገነቡ ይገኛሉ፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም ከዚህ ቀደም ያሰለጠኗቸውን ጥቂት ተጫዋቾች እና ወጣት ተጫዋቾችን አዘዋውረው የራሳቸውን ቡድን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጡት ዘላለም በአማካይ ክፍሉ የያዟቸው ይሁን እንዳሻው ፣ ዘላለም ኢሳያስ ፣ ሚካኤል ለማ እና ምስጋናው— ን የፈጠራ እና ፈጣን የማጥቃት ችሎታ በአግባቡ ከተጠቀሙበት አዝናኝ እና በርካታ ግቦች የሚያስቆጥር ቡድን መስራት ይችላሉ፡፡

በቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ በተመለከትነው የሁለቱ ቡድኖች እንቅስቃሴ ከመዘንነው በነገው ጨዋታ ለመሃል ሜዳ የበላይነት የሚደረገው ትኩረት የመስብ ይሆናል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ የሜዳውን ስፋት ተጠቅሞ ያጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግም በመስመር እንቅስቃሴ በንፅፅር ደካማ የሆነው አዳ ከተማን ይፈትናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወልድያ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በወረደበት አመት ወደ ፕሪሚር ሊጉ መመለስ የቻለው ወልድያ መልካ ቆሌ ላይ ንግድ ባንክን ያስተናግዳል፡፡ የመጀመርያውን ጨዋታ በደጋፊዎቹ ፊት ማድረጉ ወልድያን ተጠቃሚ ቢያደርገውም የቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ያላደረገ ብቸኛ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ መሆኑ ወደ ውድድር ሪትም ለመግባት የመጀመርያዎቹን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሊቸገር ይችላል፡፡   በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ያሳደገው ንግድ ባንክ አሁንም ቋሚ ተሰላፊዎቹ አምና የተጠቀመባቸው እንደመሆኑ ካለፈው የውድድር ዘመን የተለየ እንቅስቃሴ ያሳያል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በሰለሞን ገብረመድህን ምትክ ዮናስ አላባን ፤ በፊሊፕ ዳውዚ ምትክ ፒተር ኑዋዲኬን ቀጥተኛ ተተኪ አድርጎ ያስፈረሙት አሰልጣኝ ፀጋዬ በንፅፅር የተሻለ የተከላካይ ክፍል ገንብተዋል፡፡

ሀዋሳ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

ሁለቱም ቡድኖች በቅድመ ውድድር ዘመን ጨዋታዎች ካሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ በኋላ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ሀዋሳ ከተማ ጠንካራውን ተከላካይ ሙጂብ ቃሲምን አጥቶ ከሊጉ ድንቅ አማካዮች አንዱ የሆነው ፍሬው ሰለሞንን አስፈርሟል፡፡ አሰልጣኝ ውበቱ ለማጥቃት እንቅስቃሴ አመቺ የሆነ የአማካይ ክፍል ገንብተዋል፡፡ ቶጓዊው አዲስ ፈራሚ ጃኮ እና ፍርዳወቅ ሲሳይ ከአማካዮቹ ፍሬው ሰለሞን ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ጋዲሳ መብራቴ ጋር በአግባቡ ከተጣመሩ አስፈሪ የፊት መስመር መመስረት ይችላሉ፡፡

በታሪኩ የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን የሚያደርገው አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ለመሰንበት ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አመዛኑ የቡድኑ አባላት የፕሪሚየር ሊግ ልምድ የሌላቸው መሆኑ ለዋና ከተማው ክለብ ህይወት በፕሪሚየር ሊግ አስቸጋሪ ያደርግበታል፡፡ አሰልጣኝ ስዩም በከፍተኛ ሊጉ ያሳዩን ፍሰት ያለው እና በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመረኮዘ አጨዋወታቸውን በፕሪሚየር ሊጉ መድገማቸው አጠራጣሪ ነው፡፡

[table “51” not found /]

ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከተማ

በደቡብ ካስቴል ዋንጫ አንድ ምድብ የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች የውድድር ዘመናቸውን በድል ለመክፈት ይርጋለም ላይ ይፋለማሉ፡፡ የካስቴል ዋንጫው ቻምፒዮን ሲዳማ ቡና በአምናው ስብስብ ላይ ጥቂት ግን መልካም ዝውውሮችን በመፈፀም ቡድኑን ያጠናከረ ሲሆን የተከላካይ እና የአማካይ ክፍሉ የቡድኑ ጥንካሬ ነው፡፡ ቡድኑ ከመከላከል ጥንካሬው ባሻገር በማጥቃት እቅስቃሴው የፍፁም ተፈሪ የኳስ አቅርቦት የመስመር አጥቂው አዲስ ግደይ አስፈሪ ሩጫ እና ግብ የማስቆጠር ብቃት ልዩነት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

በሳምንቱ መጀመርያ ከፍተኛ ሽልማት የተበረከተላቸው የፋሲል ከተማ የቡድን አባላት በከፍተኛ ተነሳሽነት ከ8 አመት በኋላ የመጀመርያ የሆነውን የሊግ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ሁሉ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በሊግ የመቆየት ፈተናን ይጋፈጣሉ፡፡ ለፋሲል እንደጥንካሬ የሚወሰደው በሜዳው እና ውጤት የማስቀየር ኃይል ባለው ደጋፊያቸው ፊት ነጥቦች ይሰበስባል ተብሎ መገመቱ ነው፡፡

ጅማ አባ ቡና ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ጅማ አባ ቡና በታሪክ የመጀመርያውን የሊግ ጨዋታ ከአዲስ አበባ ከተማ ቻምፒዮን ጋር ያደርጋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ከሳምንት በፊት በአአ ከተማ ዋንጫ ተጫውተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡

ጅማ አባ ቡና የመጀመርያ ጨዋታውን ሞቅ ያለ ድባብ ባለው ጅማ ስታድየም ማድረጉ ተጠቃሚ ያደርገዋል፡፡ በአምናው ቡድናቸው ላይ ከፍተኛ የፕሪሚየር ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን የቀላቀሉት አሰልጣኝ ደረጄ ጥንቃቄ ላይ ያመዘነ እቅስቃሴ የሚመርጡ መሆናቸው በሊጉ ለመቆየት ዋስትና ሊሰጣቸው ይችላል፡፡

ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ያሳየው አቋም በቅርብ አመታት ያልታየ ነው፡፡ በቅድመ ውድድር ጨዋታ የቡድኖችን የሙሉ የውድድር ዘመት አቋም ለመገምገም ቢያዳግትም የአሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ ቡድን ከጨዋታ ጨዋታ ያሳየው መሻሻል እና የተጫዋቾች ግላዊ ብቃት መጎልበት እንዲሁም በቡድኑ ጠንካራ የኋላ መስመር እና ድንቅ የኳስ ክህሎት የተላበሱ አማካዮች ላይ በፊት መስመር አስፈሪ አቋም ላይ የሚገኘው አይቮሪኮስታዊው ኢብራሂም ፎፋኖ ሲታከልበት የቀድሞው ዝነኛ ቡድን መመለስን ፍንጭ የሰጠ ሆኗል፡፡

ወላይታ ድቻ ከ መከላከያ

ወላይታ ድቻ የሜዳውን ጨዋታ ይጫወትበት ከነበረው ቦዲቲ ወደ መቀመጫው ሶዶ ከተማ ተመልሶ በሶዶ ስታድየም የመጀመርያ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ከአምናው እምብዛም ለውጥ ሳያሳዩ የውድድር ዘመናቸውን ሲጀምሩ በዋና አሰልጣኝነት ሊግ ልምድ የሌለው ምንያምር ፀጋዬ በብልሁ መሳይ ተፈሪ ይፈተናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እንደተለመደው ቡድናቸውን በዝቅተኛ ወጪ መገንባታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በአምናው ቡድናቸው ላይ የብሄራዊ ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ተጫዋቾችን አክለዋል፡፡ በከፍተኛ ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወገብ ላይ በጨረሰው ነገሌ ቦረና ግብ አዳኝነቱን ያሳየው ዳግም በቀለ በተዳከመው የድቻ የአጥቂ መስመር ላይ ነፍስ ይዘራበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መከላካያ በአሰልጣኝ ምንያምር አመራር ግራ አጋቢ የቅድመ ውድድር ጨዋታዎችን አሳልፏል፡፡ የቡድኑ አይን የነበረው ፍሬው ሰለሞን መልቀቅ ትልቅ ክፍተት እንደፈጠረ ሲታይ አዳዲስ ፈራሚዎቹም በቡድኑ ላይ ጉልህ ተፅአኖ ይፈጥራሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡

bunna-vs-ded-preview

በኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት መካከል የሚካሄደውን የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ ነገ ጠዋት በስፋት ይዘን እንመለሳለን፡፡

 

 

Leave a Reply