የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ፡ ኢትዮጵያ ቡና ከ ደደቢት – ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ


ቦታ – አዲስ አበባ ስታድየም

ቀን – እሁድ ህዳር 4 ቀን 2009

ሰአት – 10፡00

ስርጭት – ቀጥታ የጽሁፍ ስርጭት በሶከር ኢትዮጵያ


 

የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመርያ ሳምንት በሊጉ እጅግ ከሚጠበቁ ጨዋታዎች አንዱን ያስመለክተናል፡፡ የሊጉ እጅግ አዝናኝ ጨዋታ 10፡00 ላይ ሲጀምር ድንቅ ድባብ ፣ የውድድር ዘመኑን በድል ለመጀመር የሚደረግ ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክርን እና ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾችን እንመለከታለን፡፡

ሁለቱም ቡድኖች በተለያየ መንገድ ቡድናቸውን አጠናክረው የውድድር ዘመኑን ለመጀመር ተዘጋጅተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና አምና አጨራረሱን ባሳመረው በድኑ ላይ ጥቂት ነገር ግን ክፍተት መሙላት የሚችሉ ተጫዋቾችን ሲያዘዋውር በድራጋን ፖፓዲች ምትክም ሌላ ሰርቢያዊ አምጥቷል፡፡ አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሲቪች ከወዲሁ በተጫዋቾቹ መወደዳቸው ለቡድኑ የውድድር ዘመን ማማር ወሳኝ ነው፡፡

የአስቻለው ግርማ መመለስ ለቡድኑ ሌላ የማጥቃት እና የግብ ማስቆጠር አማራጭ ሲሰጠው የሳሙኤል ሳኑሚ መፈረም በቡድኑ ላይ እንደክፍተት ይታይ የነበረውን የአጥቂ ክፍተት የሚደፍን ይሆናል፡፡ ዮሃንስ በዛብህ በደቡብ ካስቴል ዋንጫ ያሳየው ብቃት ከሀሪሰን ሄሱ ጋር ተደምሮ ቡና በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ እንዳይቸገር ያደርገዋል፡፡ የቡና ጠንካራ ጎን የሆኑት የተከላካይ እና የአማካይ ክፍሉ ለውጥ ያልተደረገባቸው በመሆኑ የበለጠ ተዋህደው ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ደደቢት ካለፈው አመት ቅዠት የሚመስል የውድድር ዘመን የነቃ ይመስላል፡፡ ክለቡን ወደ ቀድሞ ቦታው ሊመልሱ የሚችሉ ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች በማዘዋወር የቀድሞ አሰልጣኙን የመለሰ ሲሆን የወደፊት ኮከብ ሊሆኑ የሚችሉ ድንቅ ወጣቶንም ይዟል፡፡

ጌታነህ ከበደ የደቡብ አፍሪካ ቆይታውን አጠናቆ ወደ ደደቢት መመለስ ለሰማያዊዎቹ የውድድር ዘመን ማማር ትልቁን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡ ከጋብሬል አህመድ መልቀቅ በኀላ በአግባቡ ቦታው ያልተሸፈነው የተከላካይ አማካይ ስፍራ በአስራት መገርሳ ግዢ ተሟልቷል፡፡ የኤፍሬም አሻሞ ዝውውርም በደደቢት የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ፍጥነትን እና ቀጥተኝነትን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወጣቶቹ አቤል ያለው ፣ የአብስራ ፣ ደስታ ደሙ እና ሰለሞን ሀብቴ በአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስር እድል እንደሚሰጣቸው የሚጠበቅ በመሆኑ በውድድር ዘመኑ ጎልተው ሊወጡ የሚችሉ ወጣቶች ናቸው፡፡

 

ምን አይነት ጨዋታ እንጠብቅ?

ኢትዮጵያ ቡና በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ ደደቢት ደግሞ በ4-4-2 አሰላለፍ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና እንደከዚህ ቀደሙ በመሃል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ የሚኖረው ከሆነ ጨዋታውን የመቆጣጠር እድል ይኖረዋል፡፡ በሁለቱም ክንፎች የሚገኙት የመስመር ተከላካዮች በማጥቃት እንቅስቃሴ የሚሳተፉ በመሆኑ ቡድኑ የመሃል ለመሃል እና የመስመር እንቅስቃሴውን አመጣጥኖ መጫወት ይችላል፡፡ ነገር ግን የደደቢት ሁለቱ የመስመር አማካዮች ሽመግት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ ቀጥተኛ አጨዋወት እና ሜዳውን ወደ ጎን አስፍተው የመጫወት ዝንባሌ የቡና የመስመር ተከላካዮች ወደፊት በመሄድ በማጥቃት እንቅስቃሴ እንዳይሳተፉ ሊገድባቸው ይችላል፡፡ በአማካይ ስፍራ ደደቢት የቁጥር ብልጫ የሚወሰደበት ከሆነ የአስራት እና ሳምሶን ሚና በመከላከሉ የሚገደብ በመሆኑ አማካዩን እና አጥቂዎቹን የሚያገናኝ ተጫዋች አይኖርም፡፡ በዚህም የደደቢት የማጥቃት እንቅስቃሴ በመስመር አማካዮቹ ላይ ጥገኛ ይሆናል፡፡

ሳሚ ሳኑሚ እና ጌታነህ ከበደ

ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በደደቢት ከመስመር አጥቂነት ወደ ግብ አዳኝነት የተለወጠው ሳሚ ሳኑሚ በኢትዮጵያ ቡና ማልያ የቀድሞ ክለቡን ለመጀመርያ ጊዜ ይገጥማል፡፡ ከ2002-2005 በነበረው የደደቢት ቆይታው ኢትዮጵያ ቡና ላይ በርካታ ግቦች ያስቆጠረው ጌታነህ ከበደ ደግሞ ከ3 የውድድር ዘመናት የደቡብ አፍሪካ ቆይታ በኋላ የመጀመርያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

head-to-head

አዝናኙ ትንቅንቅ

በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች በርካታ ግቦች የሚስተናገድባቸው ናቸው፡፡ ደደቢት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገበት 2002 ጀምሮ ባደረጓቸው 14 የእርስ በእርስ ጨዋታዎች 49 ግቦች ተቆጥረዋል፡፡ በአማካይ በጨዋታ 3.5 ግቦች ማለት ነው፡፡ ከግቦቹ በተጨማሪ የሁለቱ ግንኙነት ሁልጊዜም በመሸናነፍ መጠናቀቁ ለተመልካች ምን ያህል አዝናኝ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ በሁለቱ ክለቦች መካከል የደርቢነት ስሜት ባይኖርም ጨዋታዎቹ ላይ ያለው ውጥረት እና የመሸናነፍ እልህ የደርቢ ጨዋታዎችን ያህል ለመመልከት የሚያጓጓ ነው፡፡

የቅርብ ጊዜ ግንኙነቶች

ሁለቱ ክለቦች በ2008 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባደረጓቸው ጨዋታዎች አወዛጋቢ በነበረው የመጀመርያው ዙር ጨዋታ ደደቢት 2-1 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ዙር ኢትዮጵያ ቡና በፍፁም የጨዋታ ብልጫ 3-0 አሸንፏል፡፡

 

ጨዋታውን ማን ይመራዋል?

የእለቱን ጨዋታ ኢንተርናሽናል አርቢቴር በላይ ታደሰ ይመራዋል፡፡ በላይ የ2008 የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ዳኛ ተብሎ መመረጡ የሚታወስ ነው፡፡

 

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ሀሪስን ሄሱ

አብዱልከሪም መሃመድ – ኢኮ ፊቨ – ወንድፍራው ጌታሁን – አህመድ ረሺድ

መስኡድ መሃመድ (አምበል) – ጋቶች ፓኖም – ኤልያስ ማሞ

እያሱ ታምሩ – ሳሚ ሳኑሚ – አስቻለው ግርማ

 

ደደቢት (4-4-2)

ክሌመንት አሼቲ

ስዩም ተስፋዬ – አክሊሉ አየነው – ካድር ኩሊባሊ – ብርሃኑ ቦጋለ (አምበል)

ሽመክት ጉግሳ – አስራት መገርሳ – ሳምሶን ጥላሁን – ኤፍሬም አሻሞ

ጌታነህ ከበደ – ዳዊት ፍቃዱ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *