ቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሪምየር ሊጉን በድል ጀምሯል

የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዳሜ ሲጀመር ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማ ላይ ያለውን የበላይነት ማስጠበቅ በቻለበት የሊጉ መክፈቻ የውድድር ዓመቱ ፈጣን ግብም ተመዝግቦበታል፡፡ ፈረሰኞቹ የአዞዎቹን ግብ ለመድፈር የፈጀባቸው ግዜ 30 ሰከንዶች ብቻ ነበሩ፡፡ እንግዳዎቹ ከግብ ክልላቸው ማራቅ ያልቻሉትን ኳስ ተጠቅሞ አቡበከር ሳኒ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ ኳስን ከኃላ አደራጅቶ ለመጀመር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አርባምንጮች ሲቸገሩ ተስተውለዋል፡፡

ባለሜዳዎቹ በተደጋጋሚ ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በተለይ በ31ኛው ደቂቃ ሳላዲን ሰዒድ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የመታው ኳስ የግብ አግዳሚ ሲመልስበት በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከኮትዲቯሩ ሶስያቲ ኦምኒስፖርት ደ አርሚ ወደ ፈረሰኞቹ የተዛወረው ብርኩናፋሶው አማካይ አብዱልከሪም ኒኪማ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ሳላዲን ሰዒድ የጊዮርጊስን ሁለተኛ ግብ አክሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አዞዎቹ ግብ ለማግኘት ተጭነው መጫወት ቢችሉም ጠንካራውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ ስፍራ ሳይሰብሩ ቀርተዋል፡፡ አመለ ሚልኪያስ እና ወንድሜነህ ዘሪሁን በግቡ አናት ከሰደዷቸው ሁለት ሙከራዎች ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ማግባት ዕድል እስከጨዋታው መገባደጃ አልታየም ነበር፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት አዳነ ግርማ የማሳረጊያውን ግብ በግንባር በመግጨት ከመረብ አዋህዷል፡፡ ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ3-0 አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡ የሊጉ ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ቀጥለው ይውላሉ፡፡

img_0081

img_0001 img_0035 img_0064 img_0077

 

 

1 Comment

Leave a Reply