ሶከር ኢትዮጵያ የወሩ የፕሪሚየር ምርጦችን መምረጧን ቀጥላ 3ኛ ወር ላይ ደርሳለች፡፡ የዚህ ወር ምርጦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

ለአለም ብርሃኑ

ለአለም ዘንድሮው ጠንክሮ በመጣው ሲዳማ ቡና ላይ የራሱን ድንቅ ብቃት አክሎበት ከፊቱ ካሉት ተከላካዮች ጋር የማይበገር የኋላ መስመር መስርቷል፡፡ ከፊቱ የሚገኙት ተከላካዮች ጠንካሮች ቢሆኑም በበርካታ አጋጣሚዎች ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አድኗል፡፡ ከሁሉም በላይ በዚህ ወር ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ምንም ግብ አልተቆጠረበትም፡፡

 

ሞገስ ታደሰ

በቀኝ መስመር ተከላካይነት የምናውቀው ሞገስ አሁን ወደ ጠንካራ ተከላካይነት ተለውጧል፡፡ ቡድን የመምራት እና ከጓደኞቹ ጋር ያለው መግባባትም ጎልብቷል፡፡ የቡድን ጓደኛው አወል አብደላ ሌላው በወሩ ጥሩ አቋም ያሳየ ተጫዋች ነው፡፡

 

ሳላዲን በርጊቾ

ሳላዲን ኢትዮጵያ የምትመካበት ድንቀ ተከላካይ ነው፡፡ ተከላካዩ ይህንን ዘንድሮም በሚገባ እያሳየ ነው፡፡ የጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች በየጨዋታው ቢቀያየሩም ሳላዲን ግን ከሁሉም በተሸለ የአሰልጣኙን እምነት አግኝቷል፡፡ ከሁሉም ተሰላፊ ጋር ያለው በመግባባትም ጥሩ ነው፡፡

 

አህመድ ረሺድ

ወጣቱ የኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ ዘንድሮ በሁለቱም የመስመር ተከላካይ ቦታዎች ላይ ተሰልፏል፡፡ ሮቤል በቅጣት ባልነበረባቸው ጨዋታዎች በግራ መስመር ሲሰለፍ የሰነበተው አህመድ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ደግሞ በቀኝ መስመር ተሰልፏል፡፡ ከመከላከያ ጋር በተደረገው ጨዋታ አስገራሚ ብቃትና ድንቅ ግብ አሳይቶናል፡፡ በቦታው አብዱልከሪም መሃመድ እና ዘካርያስ ቱጂ በዚህ ወር ድንቅ አቋም አሳይተዋል፡፡

 

አሸናፊ ሽብሩ

አሸናፊ አሁንም በብዙዎች እይታ ውስጥ አለመግባቱ አስገራሚ ነው፡፡ ዘንድሮ ይበልጥ ጠንክሮ የመጣው ወላይታ ድቻን የሚመራው ይህ አማካይ ነው፡፡ የተመጠኑ ረጃጅም ኳሶቹ ፣ ሸርተቴዎቹ እና የቡድኑን ፍጥነት የመቆጣጠር ችሎታው በብዙ የሊጉ አማካዮች ላይ አይታይም፡፡

 

ሙሉአለም መስፍን

ሙሉአለም በዚህ ቡድን ውስጥ ባይኖር አርባምንጭ ካለ መሪ የሚጫወት ቡደን ይሆን ነበር፡፡ የአርባምንጩ አምበል በብቸኛ የተከላካይ አማካይነት እየተሰለፈ ቢሆንም የቡድኑን እንቅስቃሴ ከኋላ ሲመራ ፣ የግብ እድሎች ሲፈጥርና የጨዋታውን ፍሰት ሲቆጣጠር ድንቅ ነው፡፡ የመከላከያው ሚካኤል ደስታ ሌላው የሚጠቀስ ተጫዋች ነው፡፡

በኃይሉ አሰፋ

በኃይሉ ልክ እንደአምናው ዘንድሮም በቅዱስ ጊዮርጊስ ውስጥ ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱን ቀጥሏል፡፡ የፈረሰኞቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያልፈው በሱ በኩል ሲሆን ከግራ መስር ተከላካዩ ዘካርያስ ቱጂ ጋር ያለው ጥምረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋነኛው የማጥቃት መሳርያ ሆኗል፡፡

 

ፍፁም ተፈሪ

ፍፁም አምና ከተደበቀበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሲዳማ ቡና ያደረገው ዝውውር እሱንም ክለቡንም የጠቀመ ዝውውር ነበር፡: ፍፁም ይበልጥ ለመከላከል ትኩረት በሚሰጠው የአሰልጣኝ ዘላለም ቡድን ውስጥ የማጥቃት እንቅስቃሴው አቀጣጣይ ነው፡፡ ግብ የማስቆጠር ፣ የግብ እድሎችን የመፍጠር እና ጨዋታ የማቀጣጠል ብቃቱ በጉልህ ታይቷል፡፡ የሀዋሳው ታፈሰ ሰለሞን በቦታው የሚጠቀስ ሌው ተጫዋች ነው፡፡

 

በረከት ገ/ፃዲቅ

የቀድሞው የሐረር ሲቲ አጥቂ እግርኳስ ሊያስቆመው ከተቃረበበት ችግር ተላቆ በድንቅ አጥቂነት ተመልሷል፡፡ በዚህ ወር አርባምንጭ ከነማ ላሳየው መሻሻልም በረከት ያሳየው አቋም የሚጠቀስ ነው፡፡ በረከት ጉልበተኛ ፣ የአየር ላይ ብቃቱ ጥሩ የሆነ የፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ አጥቂ ሲሆን እንቅስቃሴው በአመዛኙ በአማካይ ክፍል ላይ በተገደበው አርባምንጭ ውስጥ ጎልቶ ለመውጣት አልተቸገረም፡፡ ኤሪክ ሙራንዳ ሌላው በዚህ ወር ድነቅ አቋም ካሳዩ አጥቂዎች መካከል ሊጠቀስ የሚገባው ተጫዋች ነው፡፡

 

ቢንያም አየለ

ቢንያም ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ውጤት መለወጡን ተያይዞታል፡፡ በተለይም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኤሌክትሪክ በተደረጉት ጨዋታዎች አዳማ ከነማ የቢንየምን የመጨረሻ ሰአት አገልገሎት ባያገኝ ኖሮ ነጥቦች ይዞ ባልወጣ ነበር፡፡ በቡድኑ እንደ በረከት አዲሱ ያሉ ተፅእኖ የሚፈጥሩ በርካታ ተጫዋቾች ቢኖሩም እስካሁን የቢንያምን ያህል በአዳማ ውጤት ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ ያሳረፈ ተጫዋች የለም፡፡

 

ባዬ ገዛኸኝ

ባዬ በአሁኑ ወቅት የሊጉን ተከላካዮች ከሚያስፈሩ አጥቂዎች አንዱ ሆኗል፡፡ አምና ተስፈኝነቱነን ያሳየው የወላይታ ድቻ አጥቂ ዘንድሮ ይበልጥ ጎልብቷል፡፡ ከአጣማሪው አላዛር ጋር ምርጥ የአጥቂ ጥምረት የፈጠሩ ሲሆን በግሉ ጨዋታን የማሸነፍ ብቃቱም ጨምሯል፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ምርጫ ከሊጉ አጥቂዎች በባሬቶ እይታ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ አያጠራጠርም፡፡

 

ኮከብ አሰልጣኝ – ዘላለም ሸፈራው

የዘላለም ሽፈራው ቡድን የእስካሁን አካሄዱ ድንቅ የሚባል ነው፡፡ ሲዳማ ቡና የሊጉን አናት በ5 ነጥቦች ልዩነት እየመራ ሲሆን በዚህ ወር ያደረጋቸውን አራቱንም ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስተናግድ በአሸናፊነት አጠናቋል፡፡ ለዚህም አሰልጣኙ ዘላለም ሽፈራው ሊደነቁ ይገባል፡፡

 

ኮከብ ተጫዋች – ፍፁም ተፈሪ

ዘንድሮ በተጠናከረው ሲዳማ ቡና ውስጥ ፍፁም ተፈሪ ባይኖር ኖሮ በመከላከለ ላይ ጠንካራ የሆነው ቡድን በማጥቃቱ ገረድ ይቸገር ነበር፡፡ በሁለት የፊት አጥቂዎች የሚጫወተውን ቡድን ከአጥቂዎች ጋር በማገናኘት በኩል የተዋጣለት ሲሆን ወደ ኋላ አፈግፍጎ የቡድኑን የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲያቀናብርም ድንቅ ነው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የጠፋው ልጅ በሲዳማ በሚገባ አንሰራርቷል፡፡

 

 

 

ያጋሩ