ታክቲክ ፡ ቅ/ጊዮርጊስ 3-0 አርባ ምንጭ ከተማ – የቻምፒዮኖቹ የበላይነት በፕሪምየር ሊጉ ጅማሬ

የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታድየም በይፋ ሲጀመር የአምናው ቻምፒዮን ቅድስ ጊዮርጊስ አርባምንጭ ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ሶከር ኢትዮጵያም የጨዋታውን ታክቲካዊ ይዘት እንደሚከተለው ይዛላችሁ ቀርባለች።

0001

ባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደተለመደው በ 4-3-3 ቅርፅ ወደሜዳ ሲገባ በመሀል ተከላካይነት አይዛክ ኢዜንዴ እና አስቻለው ታመነ ባልነበሩበት ደጉ ደበበን እና ምንተስኖት አዳነን አጣምሯል። ሳልሀዲን ሰይድ በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ከጨረሰው አቡበከር ሳኒ እና ከበሀይሉ አሰፋ ጋር በመሆን የፊት መስመሩን ሲመሩ መሀል ላይ ናትናኤል ዘለቀ በተከላካይ አማካይነት እንዲሁም ምንያህል ተሾመ እና ቡርኪናፋሶዋዊው የቡድኑ አዲስ ፈራሚ አብዱልከሪም ኒኬማ የአጥቂ አማካይነት ሚና በመያዝ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።

የአሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬው አርባምንጭ ከተማ በአንድ አጥቂ በመጠቀም ከፊት አመለ ሚልኪያስን ሲያሰልፍ በጨዋታው መጀመሪያ የቡድኑ ቅርፅ ለ 4-2-3-1 እና ለ 4-1-4-1 የቀረበ ነበር ማለት ይቻላል። ምንተስኖት አበራ ከተከላካዮቹ ፊት በመሆን ሙሉ በሙሉ የተከላካይ አማካይነት ሚና የነበረው ሲሆን አማኑኤል ጎበና በተለይ ቡድኑ ወደ መከላከል ሲሸጋገር ከ ምንተስኖት ጎን በመሆን ሲታይ እንዲሁም ቡድኑ ኳስ ይዞ ለማጥቃት በሚሞክርባቸው አጋጣሚዎች ከ ወንድሜነህ ዘሪሁን ግራና ቀኝ ባሉት ቦታዎች ላይ በእንቅስቃሴ ሲገባ ተስተውሏል ። ይህም ሁለቱን የመስመር አማካዮች ታደለ መንገሻን እና እንዳለ ከበደን ጨምሮ ከ አጥቂው ጀርባ የነበሩትን አማካዮች ቀጥር አራት ያደርገው ነበር።

0002

ጨዋታው በተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ የተጋጣሚያቸውን የኃላ መስመር ተሰላፊዎች ስህተት በመጠቀም በአቡበከር ሳኒ አማካይነት የመጀመሪያ ጎል ያገኙት ፈረሰኞቹ በፍጥነት ወደመሪነት መምጣታቸው በጫወታው ላይ የበላይ ሆኖ ለመዝለቅ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። እንደዚህ አይነት አጋጣሚ ሲፈጠር ለተጨዋቾች ከሚጨምረው በራስ መተማመን ባለፈ ተጋጣሚን ጎል የማስቆጠር ግዴታ ውስጥ ስለሚከት እና ይዞ የሚገባውን የጫወታ እቅድም እንዲቀይር እስከማስገደድ ስለሚደርስ ውጤት ይዞ ለመውጣት ከፍተኛ እድል ይሰጣል :: ጊዮርጊሶችም ጨዋታው ሳይከብዳቸው እንዲጨርሱ የመጀመሪያዋ ጎል መገኘት አስተዋፅኦ ነበራት።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳውን የጎን ስፋት በአግባቡ እንዲጠቀም የበሀይሉ እና የአቡበከር እንቅስቃሴ ወሳኝ ነበር። ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በግራና በቀኝ በተወሰኑ ደቂቃዎች ቦታ በመቀያየር ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ቡድኑ ከመሀል ወይንም ከተከላካይ መስመሩ በተለይም ከዘካሪያስ ቱጂ በረጅሙ የሚላኩና ወደተጋጣሚው የሜዳ ክልል የሚያስገባቸውን ኳሶች ወደመስመር በማውጣት በሁለቱ የመስመር አጥቂዎች አማካይነት አደጋን የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን በተደጋጋሚ ማድረግ ችሏል። በእለቱ ከናትናኤል ፊት የነበሩት ምንያህል እና አብዱልከሪምም በሶስተኛው የሜዳ ክፍል መግቢያ ላይ የሚያገኙዋቸውን ኳሶች ወደመስመር ማሰራጨት ቀዳሚ ተግባራቸው ነበር ። ሁለቱ ተጨዋቾች ራሳቸውን ይለኳስ ነፃ በማድረግ ቡድኑ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት አማራጭ ኳስ የማቀበያ ክፍተቶችን በመፍጠር ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የታየው ሌላው ጥሩ ጎን ተጋጣሚው በራሱ ሜዳ ላይ ኳስን ተረጋግቶ እንዳይመሰርት የሚደረገው ጥረት ነበር። የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል ሜዳው አስጠግቶ ሲጫወት የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጨዋቾቹ መሀል ሚኖረውን ርቀት በማጥበብና ለተጋጣሚው ቡድን ኳስ የማቀበያ ክፍተትን ባለመስጠት እንዲሁም ኳስ በያዘው የተጋጣሚ ተጨዋች ላይ ጫናን በመፍጠር በተደጋጋሚ ኳስን ሲነጥቅ ታይቷል። እዚህም ላይ የሁለቱ ያጥቂ አማካዮች ሚና ከፍ ያለ ነበር። የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ሁለት ጎሎች እንዲሁም ሳልሀዲን በ 31ኛው ደቂቃ ላይ የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ እና አብዛኞቹ ሌሎች ሙከራዎችም ከዚህ እንቅስቃሴ ማለትም በአርባምንጭ ሜዳ ላይ ከተነጠቁ ኳሶች መነሻነት የተገኙ ነበሩ።

የአርባምንጭ ከተማ ቡድን በአመዛኙ ኳስን ከኃላ መስርቶ በመውጣት እና በበርካታ የአጫጭር ኳስ ቅብብሎች ወደተጋጣሚ ሜዳ ኳስን ይዞ በመግባት የጎል እድሎችን በመፍጠር ላይ የተመሰረት አጨዋወትን ይዞ ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስ የገጠመው። ቡድኑ በ አንድ አጥቂ እንደመጨወቱ መጠን በቁጥር በዛ ያሉ አማካዮችን በተለይም የጎል እድሎችን ለመፍጠርም ሆነ የተጋጣሚን የመሀል መስመር በልጦ ለመገኘት ጥሩ ቴክኒካዊ ብቃት ያላቸው የመስመር እና የመሀል አማካዮችን ይዟል። ነገር ግን በትናንቱ ጨዋታ ተጋጣሚው የተከላካይ መስመሩን ወደፊት አስጠግቶ መጫወቱ እነዚህ አማካዮች አብዛኛውን ጊዚያቸውን በራሳቸው ሜዳ ላይ እንዲያሳልፉ አርጓቸዋል። ብቸኛው የፊት አጥቂ አመለ ሚልኪያስም በብዛት ይገኝ የነበረው በሜዳው አጋማሽ ላይ በመሆኑ እንደልብ ለሙከራ ሚሆኑ ኳሶችን ማግኘት አልቻለም ነበር ። በዚህም የተነሳ ወደግራና ወደቀኝ በመውጣት ከአማካይ መስመሩ ጋር ለመገናኘት ሲጥር ተስተውሏል።

አርባምንጮችም ከኃላ በመቀባበል ሚያስጀምሯቸው ኳሶችም የአጥቂ አማካዮቻቸው ጋር ሳያደርሱ በተጋጣሚያቸው በሚገጥማቸው ጫና እዚያው ሜዳቸው ላይ እየተቋረጡ ለሽንፈታቸው ዋነኛ መንስኤ ሆነው ዉለዋል። በግራ እና በቀኝ የመስመር አማካይነት የተሰለፉት ታደለ እና እንዳለም ኳስን በሚይዙበት አጋጣሚዎች ወደመሀል ይዘው በመግባት ከቡድኑ ዋና ፈጣሪ ተጨዋች ወንድሜነህ ዘሪሁን ጋር ለመገናኘት ቢሞክሩም ብዙ ውጤታማ አልሆኑም ይህ ሁኔታም የቡድኑን አጨዋወት ጠባብ እንዲሆን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች በቀላሉ ጥቃቶቹን እንዲቋቋሙ አግዟቸዋል። ሁለቱ ተጨዋቾች ከ 35ኛው ደቂቃ በኃላ ቦታ ተቀያይረውም ውጤቱ ከመጀመሪያው ብዙ የተለየ አልነበረም ቡድኑም በወንድሜነህ ዘሪሁን እና በታደለ መንገሻ አማካይነት የሞከሯቸው ኳሶችም የተገኙት ከተጋጣሚያቸው ሳጥን ውጪ ነበር።

የቡድኑን አጨዋወት በተሻለ ወደጎን ለማስፋት አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉት የመስመር ተከላካዮችም በተጋጣሚያቸው ከባድ የመስመር እንቅስቃሴ ምክንያት ወደፊት ተጠግቶ የመስመር አጥቂዎቹ ከኳስ ጋር ወደ ውስጥ ሲገቡ ሚተዉትን ቦታ ለመጠቀም አልቻሉም። በዚህ ረገድ የግራ መስመር ተከላካዩ ወርቅይታደል አበበ የተሻለ ቢንቀሳቀስም በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ያረጋቸው በነበሩ ጥሩ የመስመር ሩጫዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል ድረስ ዘልቆ በመግባት ኳስ የመቀበል ምቹ አጋጣሚዎችን ቢፈጥርም ወደመሀል ከጠበበው አጨዋወታቸው የቡድን ጓደኞቹ ነፃ መሆኑን አይተው ኳስ ሳያደርሱት እየተነጠቁ እና እሱም ተመልሶ ቦታውን ሳይሸፍን ቡድኑ ለመልሶ ማጥቃት ይጋለጥ ነበር። አዳነ ግርማ በጭንቅላት በመግጨት ያስቆጠራት ሶስተኛዋ የቅዱስ ጊዮርጉስ ጎልም የተገኘችው በዚሁ በግራ በኩል ከተነሳ ኳስ ነበር።

0003

አርባምንጮች በ69ኛው ደቂቃ ገ/ሚካኤል ያቆብን በእንዳለ ከበደ ቀይረው ካስገቡ በኃላ የቡድኑ ቅርፅ ለውጥ ታይቶበታል ፡፡ ይህም ከፊት ሁለት አጥቂዎችን በማሰለፍ የመሀሉን ክፍል የዳይመንድ ቅርፅ ባለው 4-4-2 ማዋቀር ነበር ። ይህም ከቀደመው በትሻለ ቡድኑ በሁለት አጥቂዎች መጫወቱ ከፊት የተሻለ ጉልበት ሰጥቶታል በዚህም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ውስጥ ጥቂት ቢሆኑም አደጋዎችን ለመፍጠር ችሎ ነበር። ነገር ግን በዚህም ለውጥ ቡድኑ በመስመር በኩል አስፍቶ መጫወት የሚያስችለውን መንገድ ባለማግኘቱ ተጨማሪ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሳይችል እና ለውጡ የታሰበለትን ውጤት ሳያስገኝ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጪው ሳምንት ሲቀጥል እሁድ በ11፡30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን ሲገጥም አርባምንጭ ከተማ ወልድያን በሜዳው ያስተናግዳል፡፡

 

Leave a Reply