የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ታላቁ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲካሄድ ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ከፍተኛ ፉክክር፣ ጉሽሚያ እና በርካታ ግቦችን በማያጣው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ወደ ሰማያዎቹ በዝውውር መስኮቱ የተመለሰው ጌታነህ ከበደ ሃት-ትሪክ መስራት ችሏል፡
ጨዋታው በደመቀ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎቹ ድባብ ሲጀመር አደገኞቹ በመጀመሪያዎቹ 14 ደቂቃዎች ኳስን ተቆጣጠሮ በመጫወት ረገድ ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ነበሩ፡፡ በቡና መለያ የቀድሞ ክለቡን የገጠመው ናይጄሪያዊው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ የሙከረው ኳስ የቀኝ ግብ አግዳሚ በ14ኛው ደቂቃ ገጭቶበታል፡፡ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቡና የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ደደቢቶች በ15ኛው ደቂቃ የተጫዋች ቁጥር ብልጫ አግኝተዋል፡፡ የአደገኞቹ ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ሃሪሰን ሄሱ ኳስን ከግብ ክልሉ ውጪ በእጅ በመንካቱ የዕለቱ አርቢተር በላይ ታደሰ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል፡፡ በተጫዋች ቅያሪ ምክንያት ጨዋታው ለአምስት ደቂቃዎች ተቋርጧ ሲጀመር ጌታነህ ከበደ ደደቢትን መሪ ያደረገች ግብ በቅጣት ምት ከመረብ አሳርፏል፡፡
ምንም እንኳስ በቁጥር ወደ 10 ዝቅ ቢሉም ባለሜዳዎቹ አቻ የምታደርጋቸውን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ደደቢቶች በጥብቅ መከላከል እና መልሶ ማጥቃትን መተግበር መርጠዋል፡፡ ቡናዎች በተደጋጋሚ ያልተሳኩ የግብ ማግባት ሙከራዎችን በመጀመሪያው አጋማሽ ማድረግ ችለዋል፡
በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለመቀልበስ ከፍተኛ ጉጉት ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ52ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከቅርብ እርቀት በሳቆጠረው የግንባር ኳስ ሊቀዘቅዝ ችሏል፡፡ መሪነቱን ወደ 2-0 ያሰፉት ሰማያዊዎቹ አልፎ አልፎ ለዳዊት ፍቃዱ እና ጌታነህ በሚጣሉ ኳሶች ተጨማሪ ግቦች ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ አደገኞቹ በኤልያስ ማሞ፣ አቡዱልከሪም መሃመድ እና ጋቶች ፓኖም መሪነት ውጤቱን ለማጥበብ ሲጥሩ ተያተዋል፡፡
ከሶስት ዓመት የደቡብ አፍሪካ ቆይታ በኃላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ጌታነህ በ78ኛው ደቂቃ ሃት-ትሪክ የሰራበትን ግብ በስሙ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ የ2009 የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ሃት-ትሪክም ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ጨዋታው በደደቢት በኩል በርካታ ቢጫ ካርዶች የተመዘዙበት ሆኗ አልፏል፡፡ በተለየ ሶስት የደደቢት ተጫዋቾች ኤልያስ ማሞ ላይ በሰሩት ጥፋት የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ጨዋታው በደደቢት አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ያለውን የበላይነት ማስጠበቅ ችሏል፡፡
ከጨዋታ በኃላ የተሰጡ አስተያየቶች
“11 ለ10 መጫወት ለእኛ እጅግ ከባድ ነው” የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሲቪች
“ተጋጣሚያችን ጥሩ እና ጠንካራ ቡድን ነበር፡፡ እንደተመለከታችሁት መጀመሪያዎቹ 10 እና 15 ደቂቃዎ የተሻልን ነበርን፡፡ ግብ የማስቆጠር እድልን ነበረን ነገር ግን በመጀመሪያ ደደቢት ነው ማስቆጠር የቻለው፡፡ ግብ ጠባቂያችን በቀይ ካርድ ከተሰናበተ በኃላ ሁለት ወይም ሶስት የሚሆኑ የግብ ማግባት እድሎችን አግኝተን መጠቀም አልቻልንም፡፡ ደደቢቶች ሁለተኛ ግብ ሲያስቆጥሩ በእኔ አስተሳሰብ ጨዋታውን እየደመደሙት ነበር፡፡ ደጋፊዎቻችንን ማመስገን እና ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ሊጉን በአሸናፊነት ለመጀመር አስበው ነበር፡፡ በሃሪሰን ቀይ ካርድ ምክንያት እድለኛ አልነበርንም፡፡ በዚህም ምክንያት ውጤት ወደ ተቃራኒ ቡድን አምርቷል፡፡”
“አሁን ለመነጋገር አስቸጋሪ ነው (ከሃሪሰን ጋር)፤ ነገ የምንነጋጋር ይሆናል፡፡ ይህ ግዜ ለእኛ መጥፎ ነው፡፡ ደደቢት ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ 11 ለ10 መጫወት ለእኛ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ እኛ ሶስት እና አራት የሚሆኑ ጥሩ የግብ ማግባት እድሎችን ዕድለኛ ስላልነበርን አምክነናል፡፡ ደደቢቶች በአንፃሩ ወደ ግብ የሞከሩት ኳስ በሙሉ አስቆጠረዋል፡፡”
“…ዋናው ነገር ሶስት ነጥቡን ይዘን ወጥተናል” የደደቢት አሰልጣኝ ዩሃንስ ሳህሌ
“ይህ የመጀመሪያ ጨዋታችን ነበር፡፡ 29 ጨዋታ ከዚህ በኃላ ይቀራል፡፡ ሶስት ነጥቡን ይዘን ነው መውጣት የፈለግነው፡፡ ሶስት ነጥቡን አግኝተናል ነገር ግን ብዙ ስራ አለብን፡፡ ቡድኑ እስኪቀናጅ ድረስ ጌዜ ይፈጃል፡፡ ምንአልባት በአራተኛው ወይም በአምስተኛው ጨዋታ ነው የተቀናጀ ነገር የምንጠብቀው፡፡ ዋናው ነገር ሶስት ነጥቡን ይዘን ወጥተናል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ ትንሽ ለውጥ ለማድረግ ሞክረናል፡፡”
“የግብ ጠባቂው መውጣት ብዙ ጎድቷቸዋል፡፡ ይህንን ተጠቅመን ግብ ማግባታችን በራስ መተማመናችንን ከፍ እንዲያደርገው አድርጓል፡፡ ትክክለኛ ቀይ ካርድ ነው ግን የግብ ጠባቂው መውጣት ጎድቷቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡”
“ጌታነህን ከቡድኑ ለይተህ አታየውም፡፡ አጥቂ ነው፤ ግቦችን አግብቶልናል፡፡ በምንፈልገው ሰዓት የምንፈልገውን ነጥብ ይዘን እንድንወጣ አድርጎናል፡፡”