” በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ የመጀመርያ የሊግ ግቤን በማስቆጠሬ ደስተኛ ነኝ” አቡበከር ሳኒ

የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከተጀመረ አንስቶ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመስመር አጥቂ አቡበከር ሳኒ የተሳኩ ጊዜያትን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ በ2007 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ ዘንድሮ ይበልጥ የመሰለፍ እድል እያገኘ ያለው አቡበከር በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን ቅዳሜ በተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስሙን በግብ አግቢዎች መዝገብ ለማስፈር የፈጀበት ጊዜ 30 ሴኮንድ ብቻ ነበር፡፡

አቡበከር ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ የመጀመሪያውን ግብ በማስቆጠሩ የተሰማውን ደስታ ተናግሯል፡፡ ” በቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያ የመጀመርያ የፕሪሚየር ሊግ ግቤን በማስቆጠሬ ደስ ብሎኛል፡፡ የዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመርያ ግብ በእኔ በመቆጠሩም ደስተኛ ነኝ፡፡ ” ብሏል፡፡ አቡበከር አክሎም በቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ እያገኘ ስላለው የመሰለፍ እድል ምስጢር ይናገራል፡፡

” አሰልጣኛችን በእኔ ላይ እምነት በማሳደሩ ነው የቋሚ ተሰላፊነት እድሉን ማግኘት የቻልኩት፡፡ የተሰጠኝን እድል በአግባቡ ተጠቅሜ ባሳየሁት ወቅታዊ አቋም ደስተኛ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡”

img_0214

አቡበከር በውድድር ዘመኑ ቋሚ ሆኖ በተሰለፈባቸው 5 ጨዋታዎች ከግራ መስመር እየተነሳ 6 ግቦች ከመረብ በማሳረፍ ከየትኛውም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች በተሻለ መልካም ጅማሮ አድርጓል፡፡ ሁልጊዜም ጠንክሮ መስራቱ ለዚህ እንዳበቃው አቡበከር ይናገራል፡፡

” በጥሩ አቋም ላይ የተገኘሁት ሁልጊዜም ጠንክሬ እና ስራዬን አክብሬ ስለምሰራ ነው፡፡ በተጨማሪም አሰልጣኞቻችን የሚሰጡኝን መመርያ በአግባቡ ስለምተገብር ነው ጥሩ የውድድር ዘመን ጅማሮ ማድረግ የቻልኩት፡፡

” አሁን እንዴ እድል ካገኘሁ በኋላ እድሌን በአግባቡ መጠቀም የኔ ሃላፊነት ነው፡፡ እቅዴ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቋሚ ተሰላፊ መሆን ብቻ ሳይሆን የማንኛውም ተጫዋች ህልም በሆነው ብሄራዊ ቡድንም ሃገሬን መወከል እፈልጋለሁ፡፡ ያንን እድል ለማግኘትም ጠንክሬ እሰራለሁ፡፡ ” ሲል አስተያየቱን አጠቃሏል፡፡

Leave a Reply