የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጀመር ወደ ሀዋሳ ያቀናው አዲስ አበባ ከተማ በታሪኩ የመጀመርያ የሆነውን ጨዋታ 2-0 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ የጨዋታውን የመጀመርያ ታሪካዊ ግብ ከመረብ ያሰሳረፈው አማካዩ ኃይለየሱስ መልካ እና አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በጨዋታው ፣ በድሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረጉትን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
“ግብ እንደማስቆጥር አስቤ ነበር” ኃይለየሱስ መልካ
” የቡድናችንን የመጀመርያ ግብ እንደማስቆጥር አስቤው ነበር፡፡ ከጨዋታው መጀመር በፊትም ለቡድን አጋሬ እሱባለው ጌታቸው ነግርው ነበር፡፡ ቃሌን ጠብቄ ግብ ማስቆጠር ችያለሁ፡፡ ”
የመጀመርያ ግብ . . .
” አዲስ አበባ ከተማ በታሪኩ ያደረገውን የመጀመርያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ የመጀመርያውን ግብ አስቆጥሬ ታሪክ በመስራቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ግቧ ጨዋታውን ከማሸነፍ አልፎ ለቀጣይ የፕሪሚየር ሊግ ጉዟችን በቡድኑ አባላት ላይ መነሳሳት የምትፈጥር ናት፡፡ ከመጀመርያ ጨዋታችን ከሜዳችን ውጪ 3 ነጥብ ማግኘት መቻላችን ለመጪዎቹ ጨዋታዎች መነሳሳት የሚፈጥር ነው”
” . . የመጀመርያ ጨዋታችንን ማሸነፋችን ትልቅ ነገር ነው” አሰልጣኝ ስዩም ከበደ
ስለ ጨዋታው . . .
” ጨዋታው በጥሩ ድባብ እና በርካታ ተመልካች ፊት ተደርጓል፡፡ ሀዋሳዎች የመጀመርያዎቹ 25 ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጥረወብን ነበር፡፡ ሆኖም ግን የተክለማርያም ብቃት እና የተከላካዮች ጥንካሬ እኛን ወደ ጨዋታው ሪትም እንድንገባ አድርጎናል፡፡ ተጫዋቾቼም ሁኔታውን እየተላመዱት ሲመጡ ወደ እየተሻሻልን መምጣት እና ግቦች አስቆጥረን ማሸነፍም ችለናል፡፡ በጨዋታው የነበረን የቡድን መንፈስ ፣ ታክቲክ አተገባበራችን እና ቦታ አጠባበቃችን ጥሩ ነበር፡፡ ”
የመጀመርያ ድል. . .
” የተሟላ ቡድን ይዘን አልነበረም ሀዋሳን የገጠምነው፡፡ ኤፍሬም ቀሬ እና ሲሳይ ደምሴ አልነበሩም፡፡ ፍቃዱ አለሙም በተሟላ ጤንነት ላየ አይገኝም፡፡ እንደውም ግብ ማስቆጠሩ በራሱ አስገርሞኛል፡፡ ወደ ገበያው ዘግይተን በመግባታችን ለሊጉ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ለማግኘት ተቸግረን ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሲቲ ካፑ ላይ ባሳየነው እንቅስቃሴ ምክንያት የተሰጠን ግምት አናሳ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች እንዳሉ ሆነው ትልቁ አላማዬ የነበረው ተጫዋቾቼን ለጨዋታው የማነሳሳት ነበር፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ በተሳተፍንበት የመጀመርያ አመት የመጀመርያ ጨዋታችንን ማሸነፋችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሌላው አዲስ እንደመምጣታችን ልምድ ያላቸውን ቡድኖች ማሸነፍ አይቻልም የሚለውን ግምት አፋልሰን ከሜዳችን ውጪ ማሸነፋቸን ለቀጣይ ጨዋታዎች ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርልናል፡፡ “