አዲስ አበባ እግርኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ለመካፈል ከተመዘገበና በምድብ ድልድሉ ከተካተተ በኋላ እንዲሁም ተጫዋቾችን እና አሰልጣኝ ካስፈረመ በኋላ በሊጉ እንደማይካፈል መግለጹን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለክለቡ ማስጠንቂያ ልኳል፡፡
ፌዴሬሽኑ ለክለቡ በላከው ደብዳቤ አዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ቡድኑን ውድድር ካላስገባ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጃቸው የትኛውም ውድድሮች እንደሚታገድ አሳስቧል፡፡ እስከ ህዳር 17 ድረስ ክለቡ ምላሹን እንዲያሳውቅም ቀነ ገደብ አስቀምጧል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በመጪው ቅዳሜ የሚጀመር ቢሆንም በአሰልጣኝ አስራት አባተ የሚመራው አዲስ አበባ ከተማ መደበኛ ዝግጅት ማድረግ አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ክለቡ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ከአርባምነጭ ከተማ የሚያደርገው የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡