የካፍ ዋና ፀሐፊ በአዲስ አበባ የሥራ ጉብኝት አደረጉ

ይህ ዜና የደረሰን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡

ግብፃዊው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ ሂሻም አልማሪኒ በአዲስ አበባ የአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ህዳር 07/2009 ጠዋት አዲስ አበባ የገቡት ሚ/ር ሂሻም ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁኒይዲ ባሻ እና ከጊዜያዊ ዋና ፀሐፊና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ጋር በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ ተነጋግረዋል፡፡

የመጀመሪያውና ቀዳሚው ጉዳይ በመጋቢት 2009 የመጀመሪያ ሣምንት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የሚካሄደውን 39ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድን መሠረት ያደርጋል፡፡ በእዚሁ መሰረት የጉባኤው ተሳታፊዎች የሆቴል መስተንግዶና የቪዛ ጉዳዮች  ትራንስፖርትና ፀጥታ በተጨማሪም ተያያዥነት ባላቸው የጉባኤ ፕሮግራሞች የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ለካፍና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ለሆነችው አዲስ አበባና ለኢትዮጵያ መንግስት ልዩ ትርጉም ያለውና በገፅታ ግንባታ ረገድ ጠቀሜታው የጐላ በመሆኑ በድምቀትና በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ ካፍና ፌዴሬሽኑ ተቀራርበው ለመስራት ዝግጅነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ሁለተኛው የትኩረት ነጥብ በአዲስ አበባ የሚገነባው የምስራቅ አፍሪካ አካዳሚ በሁለት ዓመታት ውስጥ ተጠናቅቆ ሥራ የሚጀምርበትን ሁኔታ ይመለከታል፡፡ የካፍ ዋና ፀሐፊ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ግንባታው መጓተቱንና ጊዜ መውሰዱን ተገንዝበው፤ በቀሪ ግንባታዎች መጠናቀቅና በተጨማሪ መከናወን የሚገባቸውን ሥራዎች በተሻለ ፍጥነትና የጥራት ደረጃ ለማከናወን በሚያስችሉ መሰረት ሀሳቦች ዙሪያ የጋራ አቋም ይዘዋል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የተነሳውና የካፍ ሙሉ ድጋፍ ያገኘው ጉዳይ ከአህጉራዊ ውድድሮች መስተንግዶ ጋር ይያያዛል፡፡ በእዚሁ መሰረት በ2025 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ፌዴሬሽኑ ያቀረበውን ጥያቄ ካፍ የተቀበለው መሆኑን ተከትሎ ቀሪ ተግባራትን ለማከናወንና ከዳር ለማድረስ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በኢትዮጵያ የከተሞች እድገትና የስታድዮሞች ግንባታ መፋጠን እንዲሁም የመሠረት ልማት ግንባታዎች መስፋፋት ታላላቅ ውድድሮችን ለማስተናገድ ወሳኝነት ያላቸው ቢሆንም፤ በየከተሞቹ ግዙፍ ስታድየሞች ከመገንባት ባሻገር ጥራት ባላቸው አነስተኛ ስታዲየሞች ውድድሮች ማስተናገድ እንደሚቻል ከውይይቱ መገንዘብ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም በፋይናንስ ድጋፍ፣ በካፍ ሥራ አስፈፃሚ አህጉራዊ ውክልና፣ የኢትዮጵያ ሙያተኞች የካፍ ተሳትፎ፣ በሁለቱ ተቋማት ዘላቂ ግንኙነትና የትብብር መስኮች ላይ ያተኮሩ በዋናነትም የጋራ ተጠቃሚነትንና የእግር ኳስ ስፖርትን በማሳደግ ረገድ አይነተኛ ሚና ባላቸው መሰረታዊ ጉዳዩች ዙሪያ ጥልቅ ውይይቶች ተካሄደዋል፡፡ ሚ/ር ሂሻም ተልዕኮአቸውን አጠናቅቀው ትላንት ረፋዱ ላይ በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚካሄደውን 10ኛው የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮና ለመከታተል ወደ ያውንዴ አምርተዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *