ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገ እና ከነገ በስቲያ በሚደረጉ ስድስት የ2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡

በነገው እለት አንድ ጨዋታ ብቻ ሲደረግ 11፡30 ላይ መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ይጫወታሉ፡፡ ሁለቱም ክለቦች ፕሪሚር ሊጉን በሽንፈት የጀመሩ ሲሆን የነገው ጨዋታ አጀማመራቸውን ለማሳመር ወሳኝ ነው፡፡ ተከላካዩ አወል አብደላ ከመከላከያ ፣ ሀሪሰን ሄሱ ከኢትዮጵያ ቡና በመጀመርያው ጨዋታ ባዩት ቄ ካርድ ምክንያት የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ እና ጅማ አባ ቡና በፕሪሚር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙበት ጨዋታ እሁድ 09፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋል፡፡ አዲስ አበባ በመክፈቻው ወደ ሀዋሳ ተጉዞ በድል የተመለሰ ሲሆን ጅማ አባ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለግብ በአቻ ውጤት አጠናቋል፡፡

አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ በመክፈቻው ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም በማለም ወልድያን 09፡00 ላይ ያስተናግዳል፡፡ ወልድያ ደግሞ በመክፈቻው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ድል አስመዝግቦ በከፍተኛ መሳሳት ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡናን በ09፡00 የሚያስተናግድበት ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡ ሁለቱም የመጀመርያውን ጨዋታ ያሸነፉ ሲሆን በጥሩ አቋም ላይም ይገኛሉ፡፡

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሊጉ የመጀመርያ ድላቸውን ለማስመዝገብ 10፡00 ላይ ይፋለማሉ፡፡ ድሬዳዋ ከአዳማ በሽንፈት ሲመለስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከጅማ አንድ ነጥብ ይዞ ወደ ድሬዳዋ ተጉዟል፡፡

የሊጉ 2ኛ ሳምንት ሌላኛውን የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታን እሁድ 11፡30 በአዲስ አበባ ስታድየም ያሳየናል፡፡ ደደቢት ቅዱስ ጊዮርጊስ! ሁለቱም ክለቦች የመክፈቻ ጨዋታቸውን በተመሳሳ 3-0 አሸንፈው በከፍተኛ በራስ መተማመን ላይ የሚገኙ ሲሆን እንደከዚህ ቀደም የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ሁሉ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀዋሳ ከተማ ቅዳሜ 09፡00 ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ክብረአብ ዳዊት ድንገተኛ ህልፈት ምክንያት ለሌላ ጊዜ የተሸጋገረ ሲሆን ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ሊደረግ የነበረው የፋሲል ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታም ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ተደርጓል፡፡ የዚህ ጨዋታ መራዘም ምክንያትን ግን ፌዴሬሽኑ በይፋ አልገለፀም፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ በነገው እለት መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉትን ጨዋታ በቀጥታ የፅሁፍ ወደ እናንተ እንደምናደርስ ከወዲሁ እንገልፃለን፡፡ እሁድ ደግሞ አዲስ አበባ ከ ጅማ አባ ቡና ፣ አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና እንዲሁም ደደቢት ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉትን ጨዋታ በቀጥታ ከሶከር ኢትዮጵያ ያገኛሉ፡፡ ሁሉንም ጨዋታዎች እንደተለመደው በሶከር ኢትዮጵያ የቀጥታ የውጤት መግለጫ መከታተል ይችላሉ፡፡

 

የ2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች

[table “54” not found /]

የደረጃ ሰንጠረዥ

untitled

ከፍተኛ ግብ አግቢዎች

untitledq

Leave a Reply