ፕሪምየር ሊግ: መከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲደረግ መከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና 2 አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን ጨርሰዋል፡፡ በአንደኛው ሳምንት ሽንፈትን ያስተናገዱት ሁለቱ ክለቦች ሶስት ነጥብ ለማግኘት ከፍተኛ ፉክክር ማድረግ ችለዋል፡፡

img_0304

በሃዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ክብረዓብ ዳዊት ያልተጠበቀ ህልፈተ ህይወት ምክንያት በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት የተጀመረው ጨዋታ ብዙ የግብ ማግባት ሙከራዎችን፣ ጉሽሚያዎችን እና አራት ግቦች የተስተናገዱበት ሆኖ አልፏል፡፡ በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች አደገኞቹ የጦሩን የተከላካይ ስፍራ በተደጋጋሚ ሲፈትኑ ተስተውሏል፡፡ በተለይ ናይጄሪያዊው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ በደቂቃዎች ልዩነት ግብ ሊሆኒ የሚችሉ ሁለት እድሎችን ሲያመክን የመስመር ተጫዋቹ አስቻለው ግርማ ተከላካዮችን በማለፍ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በይድነቃቸው ኪዳኔ ሊድንበት ችሏል፡፡ ከ15ኛው ደቂቃ በኃላ በመጠኑም ወደ ጨዋታው ምት መግባት የቻሉት መከላከያዎች ከረጅም ግዜ ጉዳት በተመለሰው ምንይሉ ወንድሙ ተደጋጋሚ ያልተሳኩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ በ30ኛው ደቂቃ ምንይሉ ከቡናው ግብ ጠባቂ ዮሃንስ በዛብህ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በሚያስቆጭ መልኩ ኳሷን ወደ ውጪ ሰድዷታል፡፡ አደገኞቹ የመጀመሪው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት መሪ መሆን የሚችሉበትን እድል ሳኑሚ ከያቡን ዊልያም የተላከለትን የግንባር ኳስ ቢያገኝም ይድነቃቸው ሊያከሽፍበት ችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጫና የፈጠሩት ቡናማዎቹ ነበሩ፡፡ በ51ኛው ደቂቃ አስቻለው ወደ ግብ የመታው ኳስ በእጅ በመነካቱ የዕለቱ አርቢትር የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል፡፡   የመከላከያ ተጫዋቾች የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔውን በመቃወም አርቢትሩን ሲያዋክለቡ የተስተዋለ ሲሆን ጋቶች ፓኖም በ54ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምቱን አስቆጥሮ ቡናን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ታይቷል፡፡ ጋቶች እና ሳኑሚም ግብ መሆን የሚችሉ ያልተሳኩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ መከላከያዎች አቻ የምታደርጋቸውን ግብ ለማግኘት በይተሻ ግዛው እና ሳሙኤል ታዬ በኩል ሙከራ ያደረጉ ሲሆን የሳኑሚ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ በ63ኛው ደቂቃ መውጣት የማጥቃት ፍላጎታቸውን ጨምሮታል፡፡ ከሳኑሚ ቀይ ካርድ በኃላ የተነቃቁት መከላከያዎች አቻ ለመሆን የፈጀባቸው ግዜ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ ነበሩ፡፡ አምበሉ ሚካኤል ደስታ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ በግንባር በመግጨት ጦሩን ወደ ጨዋታው በ65ኛው ደቂቃ መልሷል፡፡

img_0600

የቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም አደገኞቹ ዳግም መሪ ለመሆን ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ መከላከያዎች መከላከልን መርጠው ነበር፡፡ በ72ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ አክርሮ ከግራ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል የመታውን ኳስ ይድነቃቸው በአግባቡ ማውጣት ባለመቻሉ የካሜሮናዊው ዊልያም በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሯታል፡፡ በ78ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሳሙኤል ሳሊሶ ያሻገረውን ኳስ ቴዎድሮስ በቀለ ወደ ግብ ቢሞክርም ዩሃንስ በድንቅ ሁኔታ አምክኖታል፡፡ ዩሃንስ የተፋውን ኳስ ከግቡ አፋፍ ያገኘው አማካዩ በኃይሉ ግርማ ወደ ግብ ቢሞክርም የግብ አግዳሚ ሊገጭበት ችሏል፡፡ ያልተጠበቀ መሪነትን የጨበጡት ቡናዎች ለአብዛኛው ደቂቃ ከመከላከያ የመጣውን ጫና ሲቋቋሙ ቢቆዩም በ88ኛው ደቂቃ በሁለተኛው አጋማሽ ይተሻን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ማራኪ ወርቁ በግንባር በመግጨት ያስቆጠረው ግብ ክለቦቹ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት እንዲያጠናቅቁ አስገድዷቸዋል፡፡

ጨዋታው ለግቦች እና በርካታ ሙከራዎች ባሻገር አላስፈላጊ ጥፋቶች ሲፈፀሙ ተስተውሏል፡፡ መከላከያ እና ኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ነጥባቸውን ማሳከት የቻሉበትም ጨዋታ ሆኖ አልፏል፡፡

 

ከጨዋታ በኃላ የተሰጡ አስተያየቶች

img_0702

“በልጆቼ የዛሬ እንቅስቃሴ በጣም ኮርቻለው” የመከላከያ አሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን

“ሁለታችንም ከሽንፈት ነው የመጣነው፡፡ ከሽንፈት ስትመጣ ደግሞ ጫና አለ፡፡ ልጆቹ ለማሸነፍ ያደረጉት ጥረት በተለይ ደግሞ ከዕረፍት በፊት (ዕድሎችን) ያለመጠቀማቸው እንጂ ከፍተኛ ተጋድሎ ነው ያደረጉት፡፡ እኔ በእንቅስቃሴያቸው በጣም ረክቻለው፡፡ ጨዋታውን እንዳያችሁት ከባድ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ቡናም መከላከያም ትልልቅ ቡድን ናቸው ስለዚህም ከባድ ጨዋታ ነበር፡፡ በተለይ በልጆቼ የዛሬ እንቅስቃሴ በጣም ኮርቻለው፡፡ (ተጋጣሚያችን) በቀይ ሲወጣበት እኛ የአጥቂ ቁጥራችንን ነበር የጨመርነው፡፡ ለዚህም ነው ግብ ማስቆጠር የቻልነው፡፡ ልጆቹ የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ስለነበረ ግብ ቢቆጠርብንም ቅያሪያችንን በማስተካከል በጥሩ እንቅስቃሴ ግቦች ልናገባ ችለናል፡፡”

“ብድናችን የአህጉራዊ ውድድር አለበት፡፡ በጉዳትም በቅጣትም የሌሉ ልጆች አሉ፡፡ ከዚህ በላይ እንሻሻላለን ብለን እናስባለን፡፡”

“(ምንይሉ ወንድሙ) ጥሩ አግዞናል፡፡ ልጁ ገና ወጣት ነው ወደፊት እየሄደ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም ከፍተኛ ናቸው፡፡ ከረጅም ግዜ ጉዳት በኃላ ነው ዛሬ ያሰለፍነው፡፡ በእንቅስቃሴው ጥሩ ነበር፡፡”

img_0695

“ሁለት ነጥብ በመጣላችን ደስተኛ አይደለሁም” የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሲቪች

“እንደማስበው ጥሩ ጨዋታ ተጫውተናል፡፡ አላውቅም ምን እንደሆነ ባላፈውም ሳምንት አንድ ቀይ ካርድ በአሁኑ ሳምንት ሌላ ቀይ ካርድ አይተናል፡፡ ሁልግዜም ቡድኔ በ10 ተጫዋች ለመጫወት ማዘጋጀት አለብኝ፡፡ ሁለት ነጥብ በመጣላችን ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ከ20 ደቂቃ በላይ በ10 ተጫዋች መጫወታችን 2 ወሳኝ ነጥቦችን አሳጥቶናል፡፡ ሁልግዜም የቁጠር ብልጫ ካላ ነገሮች ይከብዱናል፡፡”

“ስለዳኝነቱ ምን እንደምል አላውቅም፡፡ በሁለት ጨዋታ ሁለት ቀይ ካርድ ጥሩ አይደለም፡፡ ጨዋታውን ለማሸነፍ ፈልገን ነበር፡፡ ቡድኔ አጥቅቶ ተጫውቷል፡፡ አሁንም ብደግመው በ10 ተጫዋች ነው የተጫወትነው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንትም የቁጥር ብልጫ ሊኖር ስለሚችል ቡድኔን ማዘጋጀት አለብኝ፡፡”

img_0268 img_0444 img_0374

Leave a Reply