ፕሪምየር ሊግ | ፋሲል ከተማ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጣፋጭ ድል ተቀዳጅቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ቅዳሜ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ ጀምሯል፡፡ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አዳጊውን ፋሲል ከተማ አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል፡፡
ሃሪሰን ሄሱ ከአንድ ጨዋታ ቅጣት በኃላ ወደ ቋሚ አሰላለፉ ሲመለስ የከፍተኛ ሊጉ ኮከብ ተጫዋች የነበረው የፋሲል ከተማው አብዱልራህማን ሙባረክ በቅጣት ጨዋታው አምልጦታል፡፡ አብላጫ ቁጥር ያለው ተመልካች የተከታተለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አደገኞቹ የተሸላ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን ወደ እንግዶቹን የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ችለዋል፡፡ አፆዎቹ የተጋጣሚያቸው የመሃል ሜዳ ብልጫ ሳያስጨንቃቸው ለግብ የቀረቡ የተወሰኑ ሙከራዎችን በመጀመሪያው አጋማሽ ማድረግ ችለዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም አስደንጋጭ የግብ ሙከራ ያልታየ ሲሆን ሊጠቀስ የሚችለው ሙከራ በ38ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም በፋሲል ከተማ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ለካሜሮናዊው ያቡን ዊልያም ጥሩ ኳስ አመቻችቶ ቢያቀበልም ዊልያም በአስገራሚ መልኩ ኳሷን በግቡ አናት ሰድዷታል፡፡

img_0474


ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ግለት፣ በርካታ የግብ ሙከራዎችን እና አንድ ግብ የተቆጠረበት ሆኖ አልፏል፡፡ ከዕረፍት መልስ ቶጎዊው ኤዶም ሆሶሮቪ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ኤርሚያስ ሀይሉ አጼዎቹን በ49ኛው ደቂቃ መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ የተነቃቁት ፋሲሎች በተደጋጋሚ የአደገኞቹን የተከላካይ ስፍራ ሲፈትኑ አምሽተዋል፡፡ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችላቸውን ግብ ለማግኘት ሲጫኑ የነበሩት ቡናማዎቹ በ67ኛው ደቂቃ በሳዲቅ ሴቾ አማካኝነት ጥሩ አጋጣሚ ቢያገኙም የፋሲል ከተማው ግብ ጠባቂ ዩሃንስ ሽኩር ኳሷን ግብ ከመሆን ታድጓል፡፡ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ የቡናው አማካይ አማኑኤል ዩሃንስ የግብ ጠባቂው ዩሃንስ ከግብ ክልሉ መውጣቱን ተመልክቶ ከርቀት የሞከረው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ በ73ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ያሬድ ባየህ የፋሲልን ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቋርቦ የነበረ ሲሆን የመታው ቅጣት ምት የግብን ቋሚ ለትሞ ወጥቷል፡፡ የጨዋታው አርቢትር አሸብር ሰቦቃ ሁለት የባከኑ ደቂቃዎችን ብቻ መጨመራቸው ባለሜዳዎቹን ያስቆጣ ክስተት ነበር፡፡
ኤዶም፣ ኤርሚያስ፣ ሰለሞን ገብረመድህን እና አምሳሉ ጥላሁን ለፋሲል ከተማ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ቁልፍ ሚናን ተጫውተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በመጥፎ አጀማመሩ ሲቀጥል ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ፋሲል ከተማ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል አሳክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር በህመም ላይ ለሚገኘው የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ መልካም ጤንነትን ተመኝተዋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በቀኝ ትላ ፎቅ የነበሩ በውጠቱ የተከፉ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በደካማ የቡድናቸው ሊግ አጀማመር ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡


የአሰልጣኞች አስተያየት

img_0636
“ ግብ ማስቆጣር ላይ አተኩረን ጠንካራ የሆነ ልምምድ መስራት አለብን” የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሲቪች
“ምን እንደተፈጠረ አላውቅም ግን ዛሬ አስራአንድ ለአስራአንድ ሁነን ነበር የተጫወትነው፡፡ ዛሬ አምስት ወይም አራት የጠሩ የግብ እድሎችን አግኝተን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ነበር በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘን ነበር፡፡ ከአምስት እና አስር ርቀት ያገኘናቸውን ዕድሎች ነበር ስናመክን የነበረው፡፡ ብዙ የግብ ዕድሎችን እየፈጠርን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም ተጋጣሚዎቻችን ግን ሁለት ወይም ሶስት እድሎች ካገኙ ግቦችን የኛ መረብ ላይ እያሳረፉ ነው፡፡ ይህ የእኛ ትልቁ ችግር ነው፡፡”
“ሳኑሚ ባየው ቀይ ምክንያት አልተሰለፍም ስለዚህ ዊልያም በኃላ ላይ ሳዲቅን አጫውቻለው፡፡ የሚያጠቃ ቡድን ነበር ወደ ሜዳ ያስገባሁት፡፡”
“ይህ ለእኛ በጣም መጥፎ ነው፡፡ ማግኘት ከሚገባን ዘጠኝ ነጥብ አንድ ብቻ ነው ያሳከነው፡፡ ይህ ለእኔም፣ ለክለቡም እንዲሁም ለደጋፊዎችም በጣም መጥፎ ነው፡፡ ጠንካራ የሆነ ልምምድ ግብ ማስቆጣር ላይ አተኩረን መስራት አለብን፡፡”

img_0623

“በቡድን አደረጃጀት እኛ የተሻልን ነበርን” የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ
“ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ ቡና ከሁለት ጨዋታ አንድ ነጥብ ይዞ እንሚመጣ ስለምናውቅ በጫና ውስጥ ሆኖ እንደሚጫወት እናውቅ ነበር፡፡ በታክቲኩም ሜዳ ላይ ከእነሱ የተሻልን ነበርን፡፡ እነሱ ኳስ ይዘው መጫወት ነበር የሚፈልጉት እኛ ግን በታክቲኩ የበላይ ስለነበርን ማሸነፍ ችለናል፡፡ ምናልባት የፈጠርናቸውን የግብ እድሎች መጨረስ ብንችል ግቦችን መጨመር እንችል ነበር፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ጥሩ እድሎችን አግኝተው ስተዋል፡፡ በቡድን አደረጃጀት እኛ የተሻልን ነበርን፡፡ ተጋጣሚያችን ጫና ውስጥ ስለነበር ከታክቲክ ውጪ ነበር፡፡ በመልሶ ማጥቃት አንድ ግብ እንደሚያሸንፋቸው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ፡፡”
“በድቻ ጨዋታ ላይ ሶስት ነጥብ ይዘን መጥተን እንጫወታለን የሚል ስሜት ነበረን፡፡ በአጠቃላይ ከሜዳ ውጪ ኳስ መጫወት የሚችል ቡድን ነው የሰራነው፡፡ ሜዳችን ላይ ብንጫወት መልካም ነው ባይሆን እንኳን በእርግጠኝነት ከዚህ እንቅስቃሴ ወደኃላ አንልም፡፡”
“ደጋፊዎቻችን ጥሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የጠበቅናቸው ያህል አይደሉም ከዚህ በላይ ነበር የሚመጡት፡፡ የፋሲል ከተማ ሃይል እና ጉልበት ደጋፊዎቻችን ናቸው፡፡ ከነሱ ጋር ሆነን አጭር ርቀት ላይ እንቆማለን ብለን አናስብም፡፡ ወደ ህክምና የመሄድ ሃሳብ አለኝ፡፡ መሄድ ብችል እንኳን ለአጭር ግዜ ነው መሆን የሚችለው፡፡ በእርግጠኝነት ከዚህ እንቅስቃሴ አይቆምም፡፡ ልጆቹ የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ እኔ ብኖርም ባልኖርም ከዚህ እንቅስቃሴ ይወጣሉ ብዬ አላስብም፡፡”

img_0231img_0251img_0310

Leave a Reply