የ አአ ከተማ ዋንጫ በአቻ ውጤት ተከፈተ

ለ8ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲካፕ) መክፈቻ ስነ-ስርአቱ ዛሬ ተደርጓል፡፡ አዲሱ የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አማረ ማሞ በተገኙበት የተከፈተው ውድድር አንድ ጨዋታ አስተናግዷል፡፡

የአምናው ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ቡና እና የሊጉ ሻምፒዮን ደደቢት ባደረጉት የምድብ አንድ ጨዋታ ካለ ግብ 0-0 ተለያይተዋል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ በወጣት እና ተጠባባቂ ተጫዋቾቻቸው የገቡ ሲሆን ከኢትዮጵያ ቡና በኩል ምንያህል ወንድሙ(አምበል እና ጋቶች ፓኖም ሲሰለፉ ከደደቢት በኩል ከቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አንዱንም አልተጠቀሙም፡፡

ጨዋታው እጅግ ቀዝቃዛ እና በሙከራዎች ያልታጀበ ሲሆን ለወጣት ተጫዋቾቻቸው የጨዋታ ልምድ በማግኘቱ በኩል ሁለቱም ተጠቅመውበታል ማለት ይቻላል፡፡

ውድድሩ ለ5 ቀናት ሳይካሄድ ቆይቶ በመጪው አርብ እና ሰኞ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡ በምድብ አንድ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ አርብ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ