ሪፖርት | አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አንድ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከሽንፈት መልስ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማስመዝገብ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ ያለመሸነፍ ጉዞውን ለማስቀጠል ያደረጉት ጨዋታ ነበር፡፡

ባለሜዳዎቹ ኢትዮ-ኤሌክትሪኮች የመሃል ተከላካያቸው በረከት ተሰማን በቅጣት በማጣታቸው በምትኩ አምበሉን አዲስ ነጋሽ በመሃል ተከላካይነት አጫውተዋል፡፡ የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ኤሌክትሪክ የጨዋታ የበላይነት ታይቷል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛ ደቂቃ ኮትዲቯራዊው ኢብራሂም ፎፎና ከግኑ በቅርብ ርቀት ያገኘውን ዕድል ሳይጠቀምበት ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ዳዊት እስጢፋኖስ በ10ኛው ደቂቃ ለብሩክ አየለ አመቻችቶ ቢያቀብልም ቡሩክ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ የግብ ማግባት እድል በዳዊት ማሞ የተገኘ ነበር፡፡ ዳዊት ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷበታል፡፡

img_0165

በ21ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ ከግራ የፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ በአስገራሚ መልኩ ያስቆጠረው ግብ ኤሌክትሪክን መሪ አድርጓል፡፡ በጨዋታ እንቅስቃሴ የተበለጡት አዲስ አበባዎች ክለቦቹ ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸው አስቀድሞ በፍቃዱ አለሙ አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል፡፡ ፍቃዱ በጥሩ መልኩ ተመስርቶ የመጣውን ኳስ ነበር ከግብ ቅርብ ርቀት በግንባሩ በመግጨት ከመረብ ማሳረፍ የቻለው፡፡

img_0182

በሁለተኛው አጋማሽ ክለቦቹ ያገኛቸውን ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎች ሲያመክኑ ታይተዋል፡፡ በተለይ የጨዋታው መጠናቀቂያ በታቀረበበት ደቂቃ ፎፋኖ የሞከረውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆ ማምከን ችሏል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ የሊግ አጀማመሩን ሶስት ጨዋታ ባለመሸነፍ ሲያሳምር ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሸናፊ ከሆነ በኃላ በሊጉ ደካማ አጀማመር አሳይቷል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

img_0378

“ዋነኛው ችግራችን የአጨራረስ ድክመት ነው” የኢትዮ-ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ

“ብዙ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረን ነበር ከመጀመሪያው ጎል በኃላ፡፡ ግልፅ ግብ የማስቆጠር ዕድሎችን አግኝተን ነበር፡፡ ግቦቹን ብናገባ ኖሮ ውጤቱ ሌላ ነበር የሚሆነው፡፡ ያለው ዋነኛ ችግራችን የአጨራረስ ድክመት ነው፡፡ የመጀመሪያውን የሊግ ጨዋታችን ከጅማ አባ ቡና ጋር ስናደርግ ከቅርብ እርቀት ላይ ሁለት እና ሶስት የሚሆኑ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለናል፡፡ እነዚህ እድሎች መጠቀም አልቻልንም፡፡ በተመሳሳይ ከድሬዳዋ ጋርም ሶስት ወይም አራት ዕድሎችን ፈጥረን መጠቀም አልቻልንም፡፡ አሁን ያለብን እግር የአጨራረስ ነው፡፡”

“የኃላ መስመሩን እንዳያችሁት ነው፡፡ በጉዳት እና በቅጣት ሙሉ በሙሉ በሚቻል መልኩ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ በሶስት የሊግ ጨዋታችን የአማካይ ተከላካይ ስፍራ የሚጫወትልን ተጫዋችን የመሃል ተከላካይ ለማድረግ ተገደናል፡፡ ይህም ችግር አለብን ግን በዋናነት የአጨራረስ ድክመት ነው ያለብን፡፡”

img_0383

“ጥሩ በማድረጋችን ነጥብ መጋራት ችለናል” የአዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ

“እየተጓዝን ያለነው 90 በመቶ በአዲስ ተጫዋቾች እንዲሁም ከፍተኛ ሊግ ላይ በነበሩ ተጫዋቾች ነው፡፡ ከግዜ ወደ ግዜ ልምዱን እያገኙን ይሄዳሉ ማለት ነው፡፡ የዛሬውን ጨዋታ ስናየው ኤሌክትሪኮች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነውናል፡፡ ቢሆንም በመከላከሉ ጥሩ አድርገናል፡፡ ጥሩ በማድረጋችን ነጥብ መጋራት ችለናል፡፡ በአጠቃላይ ቡድናችን ከዕለት ወደ ዕለት በራስ የመተማመን ስሜት እንዲያገኝ ይህ እራሱ ብርታት ነው፡፡”

“(በአጥቂ መስመሩ ላይ) ለውጥ ለማምጣት ብንችል ደስተኛ ነን፡፡ በሁለተኛው ዙር ለውጥ ለማምጣት አንዳንድ ነገሮች ጀምረናል፡፡ ከውጭም ከሃገርም ለማምጣት ሙከራ እያደረግን ነው፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ አሁን ባለን ነው የምንጓዘው፡፡”

Leave a Reply