ሪፖርት ፡ ክብረአብ ዳዊት በታወሰበት ጨዋታ ሀዋሳ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል አሳክቷል

በ3ኛ ሳምንት የኢትዮጽያ ፕርሚየር ሊግ በደቡብ ደርቢ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ በፍሬው ሰለሞን የሁለተኛ አጋማሽ ግቦች በመታገዝ 2-0 አሸንፏል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በፊት በደረሰበት የእሳት ቃጠሎ አደጋ ምክንያት ህይወቱ ያለፈው የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠበቂ ክብረዐብ ዳዊትን በህሊና ፀሎት በማሰብ ነበር የተጀመረው ። ይህንን አሰቃቂ አጋጣሚን በማስመልከትም የሀዋሳ ከተማ ተሰላፊዎች ተጨዋቹንና በአደጋው አብረውት ያለፉት የሁለት ልጆቹን ፎቶ የያዘ ጥቁር ቲሸርት ለብሰው ወደሜዳ የገቡ ሲሆን የእንግዳው ቡድን የአርባምንጭ ከተማ ተጨዋቾችም ሀዘናቸውን በክንዳቸው ላይ ጥቁር ባንዴጅ አስረው በመጫወት ገልፀዋል። በተጨማሪም በ24 አመቱ ከዚህ አለም የተለየውን ግብ ጠባቂ በ 24ኛው ደቂቃ ላይ ደጋፊዎች በጭብጨባ እና ጧፍ በማብራት ስነስርዐት አስበውታል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ በመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች ኳስን ከኃላ መስርቶ እና ተቀራርቦ በመጫወት እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ያደረጉትን ፉክክር አስመልክቶናል።

ጨዋታው በተጀመረ በሶስተኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ በቀኝ መስመር በኩል ሞክሯት በግቡ ቋሚ በተመለሰችበት የመጀመሪያ ሙከራ ወደ ተጋጣሚያቸው የፍፁም ቅጣት ምት ክልል መቅረብ የጀመሩት ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች አብዛኛውን የመጀመሪያ አጋማሽ ክፍለጊዜ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። በአንፃሩ አርባምንጮች በተጋጣሚያቸው በኳስ ቁጥትር ቢበለጡም በመልሶ ማጥቃት ግን የተወሰኑ የጎል እድሎችን ፈጥረዋል። ከነዚህም መካከል በ22ኛው ደቂቃ ገ/ሚካኤል ያዕቆብ በቀኝ መስመር ከወንድሜነህ ዘሪሁን የተሻገረለትን ኳስ ወደግብ ሞክሮት ወደላይ የወጣበት እንዲሁም በ35ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት በግራ በኩል የተገኘውን ቅጣት ምት አሁንም ገ/ሚካኤል ያዕቆብ በቀጥታ ወደግብ ሞክሮት የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሶሶሆ ሜንሳህ ያወጣበት የሚጠቀሱ ነበሩ።

በመጀመሪያው አጋማሽ ከታዩ ትእይንቶች መካከል 40ኛው ደቂቃ አካባቢ በሜዳው አጋማሽ ላይ የአርባምንጩ ታደለ መንገሻ ኳስን በእጅ መንካቱን እና የመሀል ዳኛው በዝምታ በማለፋቸው የሀዋሳ ተጨዋቾች ዳኛውን በመክበብ እና በማዋከብ ተቃውሞቸውን የገለፁበት እና ጨዋታውም ለ 2 ደቂቃዎች ያህል የተቋረጠበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነበር። ይህ ሁኔታ በሊጎቻችን እና በብሔራዊ ቡድኖቻችን ላይ በተደጋጋሚ የሚታየው ችግር አሁንም እንዳልተቀረፈ አመላክቶን አልፏል።

15194341_1356276137745292_8893985672284562938_o

ሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ የሀዋሳ ከተማ ብልጫ የታየበት ነበር። ከእረፍት መልስ በመጀመሪያው ደቂቃ ደስታ ዮሀንስ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ቀለል ባለ አጨራራስ የመጀመሪያ ጎል አድርጎታል። ይህ ከሆነ ከ 7 ደቂቃዎች በኃላ በግራ መስመር መሳይ ጳውሎስ ወደውስጥ የጣለውን ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት ጥሩ የተንቀሳቀሰው ኤፍሬም ዘካሪያስ ሲጨርፍለት ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፍሬው ሰለሞን አግኝቶ ለራሱና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ በኃላ ይበልጥ ተዳክመው የታዩት አርባ ምንጮች በ79ኛው ደቂቃ ከ ሀዋሳ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አመለ ሚልኪያስ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ከያዘበት ሙከራ ውጪ እምብዛም አስፈሪ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም። በጨዋታ እንቅስቃሴ የበላይነታቸውን ያሳዩት ሀዋሳ ከተማዎችም ውጤቱን ሊያሰፉ ሚችሉባቸውን በርካታ አጋጣሚዎች በፍሬው ሰለሞን ፣ ፍርዳወቅ ሲሳይ ፣ ዳንኤል ደርቤ እና እስራኤል እሸቱ መፍጠር ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው 2-0 ተጠናቋል።

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

15240083_1356278871078352_587705994_n

ጨዋታውን በማስመልከት የሀዋሳው ከተማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተውናል፡-

” የመጀመሪያውን ጨዋታ መሸነፋችን እና ክብርአብን በሞት ማጣታችን እሱን ተከትሎም ቡድኑ የነበረበት ስሜት ልምምድ ለመስራት እና ለጨዋታ ዝግጁ ለመሆን ከባድ እንዲሆንብን አድርጎ ነበር። ጨዋታውንም የተጫወትነው ለክብርአብ መታሰቢያነት ነበር። በአጠቃላይ በጨዋታውም አራተኛው የሜዳ ክልል ላይ ስንደርስ ከምናባክናቸው ኳሶች በቀር ጨዋታውን ተቆጣጥረን እና በሁሉም መልኪያዎች ረገድ ተጋጣሚያችንን በልጠን ለማሸነፍ በቅተናል” ያሉት አሰልዘጣኝ ውበቱ ቡድናቸው በውድድር አመቱ ምን ሊመስል እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ” ያሉንን ወጣት ተጨዋቾች ከነባሮቹ ጋር በማቀናጀት ኳስ ላይ መሰረት ያደረገ ቡድንን ለመስራት ሂደት ላይ ነን፡፡ በዚህም አቅማችን የፈቀደውን ውጤት ለማምጣት እንጥራለን” ብለዋል።

15239404_1356278787745027_418294359_n

የአርባምንጭ ከተማው ረዳት አሰልጣኝ ግርማ ካሳዬ በበኩላቸው የሽንፈታቸው ምክንያት ያገኙን አጋጣሚ በአግባቡ አለመጠቀማቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

” ከሜዳችን ውጪ በመጨወታችን በአንድ አጥቂ ነበር የተጠቀምነው፡፡ ያም ሆኖ የፈጠርናቸውን ጥቂት የጎል እድሎች ቢኖሩም መጠቀም አልቻልንም ነገር። ነገር ግን በጥቅሉ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል” ብለዋል ክለቡ ከ3 ጨዋታዎች 1 ነጥብ ብቻ በማግኘት አምስት ጎሎችን አስተናግዶ በሊጉ መጥፎ ጅማሬ ማረጉን አስመልክቶ በመጪው ጨዋታዎች ያላቸውን እቅድ አሰልጣኝ ግርማ እንዲህ አብራርተዋል፡፡ “በተከላካይ መስመር ላይ ያለብንን ችግር ከጉዳት በሚመለሱ ተጨዋቾች በመቅረፍ በሜዳችን በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ነጥብ ለመሰብሰብ እንሞክራለን ”

 

Leave a Reply