በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታ መልካ ቆሌ ላይ ደደቢትን ያስተናገደው ወልድያ ለ3ኛ ተከታታይ ጨዋታ መረቡን ሳያስደፍር ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡
በቁጥር እጅግ በርካታ የነበረው የወልድያ ደጋፊ ከጨዋታው አንድ ሰአት ቀድሞ ነበር ሜዳውን መሙላት የቻለው፡፡ ጨዋታውም ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተሸለ በሞቀ ድባብ ተካሂዷል፡፡
በጨዋታው ደደቢት በኳስ ቁጥጥር ተሽለው የታዩ ሲሆን የወልድያ የተከላካይ ክፍልም የዋዛ አልነበረም። በ14ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር በኩል ሽመክት ጉግሳ ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ ወደ ጎል ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ እንዲሁም የወልድያው አማካይ ዳንኤል ደምሴ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የደደቢት ተጫዋቾችን በማለፍ ወደ ጎል በረዥሙ የሞከረው ኳስ በጨዋታው የመጀመርያ 20 ደቂቃዎች ከታዩ ሙከራዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ጨዋታው ውጥረት የነገሰበት እና ሀይል የተቀላቀለበት የነበረ ሲሆን በ24ኛው ደቂቃ በኤፍሬም አሻሞ እና ምንያህል ይመር መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት እና የቃላት ልውውጥ የዚህ ማሳያ ነበር።
በ30ኛው ደቅቃ ሽመክት ጉግሳ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ጎል ቢመታውም በሊጉ ጥንካሬውን እያሳየ የሚገኘው ካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ ቤሊንጌ አድኖታል። ለእረፍት ጥቂት ሰከንዶች ሲቀሩ በመጠኑም ቢሆን የዳኛን ውሳኔ በመቃወም የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈት ቢታይም በወልድያው አንበል ዮሀንስ ሃይሉ እና ተከላካዩ አዳሙ ሙሀመድ ደጋፊውን በማረጋጋት ሊበርድ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ የደደቢት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የቀጠለ ሲሆን እንደመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም የግብ ሙከራዎች ግን አልነበሩም፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሐብቴ በግራ መስመር በኩል ያሻማውን ኳስ ጌታነህ ተቆጣጥሮ ሲሞክር ቢሌንጌ ግብ ከመሆን ያገደው ኳስ ብቻ በሁለተኛው አጋማሽ ሊጠቀስ የሚችል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር፡፡
ውጥረት እና ሽኩቻ በሁለተኛውም አጋማሽ የተስተዋለ ሲሆን በ69ኛው ደቂቃ በወልድያው የቀኝ መስመር ተከላካይ ቢኒያም ዳርሰማ እና ጌታነህ ከበደ መካከል በተፈጠረ ግጭት የእለቱ ዳኛ ለሁለቱም የማስጠንቀቂያ ካርድ መዘዋል። ጨዋታው በአጠቃላይ የደደቢት የእንቅስቃሴ እና የወልድድያ ጠንካራ የተደራጀ እንቅስቃሴ እንዲሁም አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች እና ጉሽሚያዎች የተስተዋሉበት ነበር።