ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ በተሰለፈበት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ክለቡ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ታላል ኤል ጋይሽን ከሜዳው ውጪ በጋዛል ኤል ሪያዳ ስታዲየም ገጥሞ 3-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሙሉውን የጨዋታ ግዜ ከቀኝ መስመር በመነሳት የተጫወተው ኡመድ በአዲስ ክለቡ የመጀመሪያ የሊግ ግቡንም ማስቆጠር ችሏል፡፡
አህምድ መግዲ ክለቦቹ ወደ መልበሻ ቤት ከማቅናታቸው አስገድሞ የግብፅ የጦር ሚኒስቴሩን ክለብ ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡ ኡመድ በ51ኛው ደቂቃ በቀኝ እግሩ የፍፁም ቅጣት ምቱ ክልል ላይ የመታው ኳስ የኤሳም ሶብሂ መረብ ላይ አርፏል፡፡ የኤል ሃርቢን ሶስተኛ ግብ ሳላ አሚን ከዋሊድ ሃሰን የተቀበለውን ኳስ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል፡፡ ለኤል ጋይሽ የመ፣ስተዛዘኛውን ግብ የቀድሞ የዛማሌክ ኮከብ አህመድ ኢድ በፍፁም ቅጣት በ82ተኛው ደቂቃ በስሙ አስመዝግቧል፡፡
ኡመድ ከሁለት ዓመት በኃላ በኢትሃድ አሌክስአንደሪያ መለያ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ላይ ግብ ሲያስቆጥር ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ በዓመቱ መጀመሪያ ኤንፒን ለቆ በታዋቂው አሰልጣኝ ሻውኪ ጋርቢ ወደ ሚሰለጥነው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በአንድ ዓመት ውል የመጣው ኡመድ በተደጋጋሚ በቋሚ አሰላለፉ ውስጥ በመግባት ላይ ይገኛል፡፡
የግብፅን ፕሪምየር ሊግ አል አሃሊ በ29 ነጥብ ሲመራ ምስር ኤልማቃሳ በ27 ሁለተኛ ነው፡፡ በኤል ማቃሳ ሽንፈት የደረሰበት የሽመልስ በቀለው ፔትሮጀት በ22 ነጥብ አራተኛ ሲሆን ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በዘጠኝ ነጥብ 13ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በአስራ ሁለተኛው ሳምንት ፔትሮጀት ሰሞሃን በሜዳው ማክሰኞ ሲያስተናግድ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ሐሙስ ኤል ናስር ታድን ይገጥማል፡፡
የኡመድን ግብ ለመመልከት ይህንን ሊንክ ይከተሉ https://www.facebook.com/stadmasreg/videos/1854744011479275/