የሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ ዘንድሮ አይካሄድም

አመታዊው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ክለቦች ዋንጫ ከ2010 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ዘንድሮ እንደማይካሄድ ታውቋል፡፡ የአዘጋጅ ሃገር እጦትም ለውድድሩ መሰረዝ እንደምክንያት ተነስቷል፡፡

ታንዛንያ የ2016 ውድድርን እንድታስተናግድ ተመርጣ የነበረ ቢሆንም በውድድሮች ጫና ምክንያት እንደማታስተናግድ ማስታወቋን ተከትሎ ውድድሩ በያዝነው ወር በኬንያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር፡፡ ሆኖም ኬንያም ውድድሩን ማስተናገድ እንደማትችል በማስታወቋ የዘንድሮው የሴካፋ ክለቦች ዋንጫ እጣ ፈንታ ሳይካሄድ መቅረት ሆኗል፡፡ በዚሁ የአስተናጋጅ እጦት ምክንያትም በብሄራዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የሴካፋ ሲንየር ቻሌንጅ ካፕ ዘንድሮ የመካሄድ እድሉ እየተመናመነ መጥቷል፡፡

የ2015 የካጋሜ ዋንጫ በታንዛንያ አስተናጋጅነት መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን አዳማ ከተማ ተካፋ በነበረበት ውድድር የታንዛንያው አዛም የኬንያው ጎር ማሂያን አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች የሚሳተፉበት ስታር ታይምስ የተሰኘ የዋንጫ ውድድር በታንዛንያ አስተናጋጅነት ከዲሴምበር 16 ጀምሮ ይካሄዳል፡፡ ስታር ታይምስ ስፖንሰር ባደረገው ውድድር 6 የምስራቅ አፍሪካ እና 2 የመካከለኛው አፍሪካ ክለቦች ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን በውድድሩ ላይ የኢትዮጵያ ክለቦች አልተጋበዙም፡፡

በዚህ ውድድር ላይ የኬንያም ቻምፒዮን ጎር ማሂያ ፣ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ባለድሉ ቲፒ ማዜምቤ ፣ የዩጋንዳው ቻምፒዮን ኬሲሲኤን ጨምሮ 2 የታንዛንያ ፣ 1 የቡሩንዲ እና የሞዛምቢክ ክለቦች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

ውድድሩን ለሚያሸንፍ ክለብ 50ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት ሲዘጋጅለት ለኮብ ተጫዋች እና ግብ ጠባቂ 2000ሺህ ዶላር ተዘጋጅቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *