አሰልጣኝ ደረጄ እና ዳዊት ተፈራ ስለ ጅማ አባ ቡና ታሪካዊ ድል እና ጎል ይናገራሉ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት በሜዳው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናገደው ጅማ አባ ቡና 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ይህም ለጅማው ክለብ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ የመጀመርያው ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ዳዊት ተፈራ በ50ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ግብም ለክለቡ የመጀመርያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በጅማ አባ ቡና የመጀመርያ ድል እና ጎል ዙርያ ሶከር ኢትዮጵ ከሰልጣኝ ደረጄ በላይ እና ግብ አስቆጣሪው ዳዊት ተፈራ ጋር ያደረገችውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

‹‹ የጎሉ መታሰቢያነት ለክብረዐብ ዳዊት ይሁንልኝ›› ዳዊት ተፈራ

ስለ መጀመርያ ግቡ

‹‹ በጅማ አባ ቡና የፕሪሚየር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያው ጎል አስቆጣሪ በመሆኔ የፈጠረብኝ ስሜት በጣም የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ጎል አላስቆጠርንም ነበር፡፡ በተጨማሪም ህዝቡ ውጤት ስለሚፈልግ ማሸነፍ ነበረብን፡፡ ያንን ለማድረግ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው፡፡ ይህም ተሳክቶ የመጀመርያ ጎል በኔ ተቆጥሮ በማሸነፍችን ተደስቻለሁ፡፡ ለጅማ አባ ቡና በኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመርያው ተሳትፎ ላይ ቀዳሚውን ጎል እኔ በማስቆጠሬ እጅግ በጣም ተደስቻለው፡፡››

ቀጣይ ጉዞ

‹‹ አሁን ወደ አሸናፊነት ተመልሰናል እኔም ሆንኩ የቡድን አጋሮቼ አሰልጣኛችን የሚሰጠንን ስራ በሚገባ ሰርተን ጅማ አባቡናን በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እናደርገዋለን ብዬ አስባለው››

መታሰቢያ . . .

‹‹ ይህችን ታሪካዊ ጎል መታሰቢያነቱ በቅርቡ በአሳዛኝ ሁኔታ ከነ ልጆቹ ላጣነውና በ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አብሮኝ ለተጫወተው ለሀዋሳው ግብ ጠባቂ ክብረአብ ዳዊት መታሰቢያ ይሁንልኝ ››

img_2260

‹‹ እውነት ለመናገር ከፕሪሚየር ሊጉ ይልቅ ከፍተኛ ሊጉ በጣም ፈታኝ ነው›› አሰልጣኝ ደረጄ በላይ

ስለ ጨዋታው

‹‹ እውነት ለመናገር ከፕሪሚየር ሊጉ ይልቅ ከፍተኛ ሊጉ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ አልከበደንም ፤ ምንም የተለየ ነገርም አላየሁበትም፡፡  ሆኖም በሁለቱ ጨዋታ ላይ ጎል አለማስቆጠራችን እንጂ ቡድኔ በግብ ጠባቂ በኩል ፣ በመከላከሉ ፣ በእንቅስቃሴ በጣም መልካም የሚባል እንቅስቃሴ ነው የሚያደርገው፡፡ ጨዋታውን ከሙሉ የጨዋታ ብልጫ ጋር አሸንፈን ወጥተናል ። ጎል ማስቆጠር ላይ ነበር ችግራችን ፤ ነገር ግን እሁድ ተሳክቶልን ጎል ወደ ማስቆጠሩ ተመልሰናል››

ስለ መጀመርያ 3 ነጥብ

‹‹ በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ አንድ ነገር ለማድረግ ሞክረህ አልሳካ ብሎ ሲቀርና እንደገና በጥረትህ ስታገኘው እንዴት ደስ እንደሚል ለመግለፅ ከባድ ነው፡፡ ጅማ አባቡና በታሪክ የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ በማስመዝገቡ በጣም ተደስቻለው፤፤ ››

ስለ ቡድናቸው

‹‹ ቡድኔ ልምድ ባላቸው እና  በወጣቶች የተሞላ ነው፡፡ በታክቲካል ዲሲፕሊን ላይ በጣም ጥሩ ናቸው፡፡  በአጨዋወታችንም ላይ የታክቲክ ለውጥ አድርገናል፡፡ በፊት ረጃጅም ኳሶችን ነበር የምንጠቀመው፡፡ አሁን ተጠጋግተን በመጫወት ቡድኖችን ጫና ውስጥ መክተት እንዳለብን እንዲሁም ጎል ማስቆጠርን ከአጥቂዎች መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከአማካዮች ጎል ለማግኘት በሚገባ እየሰራን ነው። አሁን  ወደ አሸናፊነት እና ጎል ወደ ማስቆጠር ተመልሰናል፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት ቀሪ ጨዋታዎች ለማሸነፍ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ››

Leave a Reply