ደደቢት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን አሰናበተ

ደደቢት እግርኳስ ክለብ ከአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጋር ተለያቷል፡፡ አንጋፋው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌም ቀጣዩ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው እንደሚሾሙ ይጠበቃል፡፡

ደደቢት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣን ስንብትን እስካሁን ይፋ ባያደርግም ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ አካባቢ ባገኘችው መረጃ መሰረት አሰልጣኝ ዮሃንስ ከደደቢት አሰልጣንነታቸው ተነስተዋል፡፡ በዛሬው እለት የነበረውን የክለቡ ልምምድንም ረዳት አሰልጣኙ ኤልያስ ኢብራሂም እንደመራው ታውቋል፡፡

በደደቢት የቴክኒክ ዳሬክተርነት እያገለገሉ የሚገኙት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ዮሃንስ ሳህሌን ተክተው የሰማያዊዎቹ አሰልጣን እንደሚሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን በመጪው ቅዳሜ ሀዋሳ ከተማን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ቡድኑን ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከተጀመረ ገና 3 ሳምንት ብቻ ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ደደቢት አሰልጣኑን በማሰናበት ቀዳሚው ክለብ ሆኗል፡፡

ደደቢት ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ የውድድር ዘመኑን በድል ቢጀምርም በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፎ ከወልድያ ነጥብ ተጋርቶ በደረጃ ሰንጠረዡ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply