ጋቦን በጥር 2017 ለምታስተናግደው የቶታል አፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት እንዲረዳቸው የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ‘ሚቾ’ 40 ተጫዋቾችን ዛሬ ይፋ አድርገዋል፡፡ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚጫወቱ አራት ዩጋንዳዊያን መካከል ሶስቱን በቡድናቸው ስብስብ ውስጥ አስገብተዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሮበርት ኦዶንካራ፣ አይዛክ ኢዜንዴ እና ያስር ሙገርዋን ሲጠሩ ለጅማ አባ ቡና በቋሚነት ላይ በመጫወት የሚገኘው አማካዩ ክሪዝስቶ ንታሚቢ ከምርጫው ውጪ ሆኗል፡፡ ኦዶንካራ የፕሪምየር ሊጉ መክፈቻ ሃገሩ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በነበረባት ጨዋታ ምክንያት ሳይሰለፍ ቢቀርም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን እና መከላከያን በረታበት ጨዋታዎች የፈረሰኞቹን ግብ ጠብቋል፡፡ በተሰለፈባቸው ሁለት ጨዋታዎችም ግቦች አልተቆጠሩበትም፡፡
ያስር ሙገርዋ በሊጉ አንድም ጨዋታ ያላደረገ ሲሆን በሚቾ ስብስብ ውስጥ መካተት ችሏል፡፡ በካፍ ግሎ በአፍሪካ የሚጫወት የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ዕጩ ውስጥ የገባው ዴኒስ ኦኒያን፣ አጥቂው ፋሩክ ሚያ ሌሎች የተካተቱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሚቾ ስለምርጫው እንዳሉት ከሆነ ሁሉም ተጫዋቾች የመጨረሻ 23ቱ ውስጥ ለመግባት ዕኩል ዕድል አላቸው፡፡
“የ40 ተጫዋቾች ስብስብ የያዘ ቡድን አሳውቀናል፡፡ 5 ግብ ጠባቂዎች፣ 12 ተከላካዮች፣ 15 አማካዮች እና 8 አጥቂዎች የመጨረሻዎቹ የ23ቱ ስብስብ ውስጥ ቦታ ለማግኘት እና ዩጋንዳን ከ39 ዓመታት በኃላ በጋቦን 2017 የአፍሪካ ዋንጫ ለመወከል ይፎካከራሉ፡፡” ይላሉ ሚቾ፡፡
ሚቾ አያይዘውም ብድናቸው ልምድ ያላቸው እና ወጣት ተጫዋቾችን መያዙን ይገልፃሉ፡፡ “የመረጥነው ልምድ ያላቸው እና የዩጋንዳ እግርኳስ የወደፊት ተስፋዎች የሆኑ ወጣት ተጫዋቾች ድብልቅ ነው፡፡ ማንም በስጦታ መልክ ይሁን በማንኛው መንገድ በአፍሪካ ዋንጫው ቡድን ውስጥ ቦታ አይሰጠውም፡፡ አሁን ቆጣሪው ከዜሮ ነው የሚጀምረው፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች በጤናማ ፉክክር የመጨረሻዎቹ 23ቱን የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡”
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ዴኒስ ኢኒያጎ
ሮበርት ኦዶንካራ
ጀማል ሳሊም
ኢስማኤል ዋቴንጋ
ቤንጃሚን ኦቻን
ተከላካዮች
ዴኒስ ኢጉማ
ጆሴፍ ንሱቡጋ
ኒኮላስ ዋዳዳ
ጆሴፍ ኦቻያ
ሻፊክ ባታምቡዚ
አይዛክ ኢዜንዴ
ሙሩሺድ ጁኮ
ሮናልድ ሙኪቢ
ቲሞቲ አዋኒ
ሪቻርድ ካሳጋ
ካሊድ ልዋሊዋ
ራሺድ ቶሃ
አማካዮች
ካሊድ አዉቾ
ቶኒ ማዊጄ
ሃሰን ዋሳዋ
ማይኪ አዚራ
ጂኦፍሪ ኪዚቶ
ኬዚሮን ኪዚቶ
ሙዛሚል ሙትያባ
ያስር ሙገርዋ
ጁማ ሳዳም
ሞሰስ ኦሎያ
ዊሊያም ሉዋጋ ኪዚቶ
ጎድፍሬ ዋሉሲምቢ
ፓል ሙኩርዚ
ማርቲን ኪዛ
ታቡ ቪታሊስ
አጥቂዎች
ፋሩክ ሚያ
ጅዮፍሪ ማሳ
ጅዮፍሪ ሴሬንኩማ
መሃመድ ሻባን
ዩኑስ ሴንታሙ
ዴሪክ ንሲባምቢ
ኢድሪሳ ሉቤጋ
ኢሪሳ ሲኪሳምቡ