ፍቅሩ እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ ድረስ ለዊትስ ለመጫወት ተስማማ

የአትሌቲኮ ዲ ካልካታው አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ ከደቡብ አፍሪካው ክለብ ቢድቬትስ ዊትስ ጋር እስከ 2014/15 የውድድር ዘመን ፍፃሜ ድረስ ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል፡፡

ፍቅሩ ከህንዱ ክለብ ጋር በአዲሱ የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግ ጥሩ የውድድር ዘመን ያሳለፈ ሲሆን እስከ ቀጣዩ የውድድር ዘመን መጀመርያ ድረስ ያለውን ሰፊ ጊዜ ካለጨዋታ ለማሳለፍ ይገደዳል፡፡ በዚህም ምክንያት በአብሳ ፕሪሚየር ሺፕ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለው ቢድቬትስ ዊትስን ተቀላቅሎ የውድድር ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለመቆየት ተስማምቷል፡፡

ፍቅሩ በአዲሱ ክለቡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ጌታነህ ከበደን የሚያገኝ ሲሆን ከዚህ ቀደም በሱፐር ስፖርት ዩናይትድ ካሰለጠኑትና መልካም ግንኙነት እንዳለው ከሚነገርላቸው ጋቪን ሃንት ጋርም በድጋሚ ይገናኛል፡፡

ቢድቬትስ ዊትስ በ2015 የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ላይ ቢካፈልም የተጫዋቾች የምዝገባ ጊዜ በመጠናቀቁ ፍቅሩ ዊትስን የሚያገለግለው በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ በሚገኙበት አብሳ ፐሪሚየር ሺፕ እና በኔድካፕ ውድድር ላይ ብቻ ነው፡፡

ያጋሩ