ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ | ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

ውድድር ፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት

ቀን : እሁድ ህዳር 25 ቀን 2009

ሰአት ፡ 09:00

ቦታ : ይርጋለም ስታድየም , ይርጋለም

ስርጭት : ቀጥታ የጽሁፍ ስርጭት በሶከር ኢትዮጵያ


ወላይታ ድቻ በ2006 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ ወዲህ በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች የጋለ የፉክክር እና የደርቢነት መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው ሆነዋል፡፡ የሞቀ የስታድየም ድባብ ፣ የደጋፊዎች ብሽሽቅ እና የሜዳ ላይ ጉሽሚያ የጨዋታው አካል እየሆነም መጥቷል፡፡ ሁለቱም መልካም የውድድር ዘመን ጅማሬ ማድረጋቸውን ተከትሎም ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

የውድድር ዘመን አጀማመር

ሁለቱም በሜዳቸው ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በድል በመወጣት ተመሳሳይ 6 ነጥቦች ሰብስበዋል፡፡ የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ባለድሉ ሲዳማ ፋሲል እና ድሬዳዋን ጋብዞ በተመሳሳይ 1-0 ሲያሸንፍ ወደ አዳማ ተጉዞ 2-0 ረሸንፎ ተመልሷል፡፡ ዘንድሮ ወደ ዋና መቀመጫው ሶዶ ተመልሶ ጨዋታ ማድረግ የጀመረው ድቻ ደግሞ መከላከያ እና አዳማን በተመሳሳይ 2-0 ሲረታ ከፋሲል ከተማ ጋር ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል፡፡ ሲዳማ በንፅፅር ፈታኝ የሆነውን ቡድን ሲያስተናግድ ድቻ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ፈተናውን ይጋፈጣል፡፡

ጥንካሬ እና ድክመት

ሲዳማ ቡና ትልቁ ጥንካሬ የተከላካይ እና የአማካይ መስመሩ ነው፡፡ ለአለም ብርሃኑ ከተከላካዮች ጋር ያለው ጥምረት እንዲሁም አማካዮቹ ለተከላካይ ክፍሉ የሚሰጡት ሽፋን ሲዳማ ቡና ብዙ ግብ እንዳያስተናግድ ያደርጉታል፡፡ ነገር ግን ሲዳማ ቡና ዘንድሮም የአጥቂ መስመሩን ሳያድስ በመቅረቡ ብዙም ክፍተት በማይሰጠው ድቻ ሊፈተን እና ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል፡፡

ወላይታ ድቻ ዘንድሮም በጠንካራ የቡድን እና የአሸናፊነት መንፈስ መልካም አጀማመር ማድረግ ችሏል፡፡ አሰልጣኘ መሳይ ተፈሪ የቡድኑ ሁሉ ነገር እንደሆኑ ዘንድሮም እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ ቡድኑ እንደ ሲዳማ ቡና ሁሉ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ቢኖረውም የአጥቂ መስመሩ በሚገባ የተደራጀ አይደለም፡፡

ቁልፍ ተጫዋቾች

አዲስ ግደይ በምርጥ አቋሙ ላይ ከተገኘ የትኛውም ቡድን ላይ አደጋ መፍጠር እንደሚችል ከአምና ጀምሮ እያሳየን ይገኛል ፤ በዛብህ መለዮ 2 ግብ አስቆጥሮ 1 ለግብ የሆነ ኳስ በማመቻቸት በሊጉ ድንቅ አጀማመር ካሳዩ ተጫዋቾች ተርታ ተሰልፏል ፤ የአንተነህ ተስፋዬ እና አበበ ጥላሁን ጥምረት በቀላሉ የማይሰበር ሆኗል ፤ አንጋፋው አላዛር ፋሲካ ድቻን እየመራ እና ግብ እያስቆጠረ ይገኛል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች በጨዋታው ውጤት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ሊያሳርፉ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ናቸው፡፡

picsart_1480745751600

ርስ በእርስ ግንኙነት

ወላይታ ድቻ በ2006 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች 6 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ሲዳማ 3 ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ 1 ድል አስመዝግቧል፡፡ ቡድኖቹ ይርጋለም ላይ ባደረጓቸው 3 ጨዋታዎች ደግሞ ሲዳማ ቡና ሶስቱንም በማሸነፍ 100% ሪኮርድ መጨበጥ ችሏል፡፡

ስለጨዋታው ምን ተባለ?

በጨዋታው ዙርያ ሶከር ኢትዮጵያ የሁለቱን ቡድን አሰልጣኞች እና ተጠባቂ ተጫዋቾችን አስተያየት እንደሚከተለው አጠናቅራለች፡፡

” ወደ ሜዳ የምንገባው የማሸነፍ ብቻ አላማ ይዘን ነው” አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ

# ዝግጅት

” የተለየ ያደረግነው ዝግጅት የለም፡፡ የአመቱ መጀመርያ ላይ ለማንኛውም ቡድን የሚሆን ዝግጅት አድርገናል፡፡ የደርቢ ጨዋታ ግርግር ፣  ውጥረት እና ውበት የተሞላበት እንደመሆኑ መጠን ጥሩ ፉክክር ጥሩ እግርኳስ እናይበታለን፡፡ ባለሜዳ እንደመሆናችንም መጠን ወደ ሜዳ የምንገባው ለማሸነፍ ብቻ ነው፡፡   ”

#በሜዳቸው የማሸነፍ ሪኮርድ ስለማስጠበቅ

” ያንን አስጠብቀን ለመሄድ እናስባለን፡፡ ቡድኔ ወደ ጥሩ አቋም እየመጣ ነው፡፡ ያሉብንን ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት እያስተካከልን እየመጣን ነው፡፡ አሁንም የግብ እድሎችን የመጨረስ ችግር አለብን፡፡ ያንን አስተካክለን እንሰራለን ብዬ አስባለው፡፡ ”

” 90 ደቂቃው ካለፈው ታሪክ የበለጠ ጠቃሚ ነው” አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ

# ስለ ጨዋታው

“የጨዋታው ሰአት ሲደርስ የምናየው ቢሆንም ጠንካራ ፉክክር እና ጥሩ ጨዋታ እናያለን ብዬ እጠብቃለው፡፡ እነሱ ሁለት አሸንፈው አንድ ተሸንፈዋል፡፡ እኛ ደግሞ ሁለቱን ጨዋታ አሸንፈን አንድ ጨዋታ ይቀረናል፡፡ ያው ሁሉን ነገር ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የምናየው ይሆናል፡፡

# ድቻ ይርጋለም ላይ ያለውን ሪከርድ ስለመቀየር

” ታሪክ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሆኖ መገኘት ነው የሚበልጠው፡፡ በተጨማሪም ሲዳማ ቡናዎች እኛ ሜዳ መጥተው አሸንፈውን አያውቁም፡፡ በአጠቃላይ ውጤቱን የሚወስነው የዘጠና ደቂቃው ፍልሚያ እንጂ ያለፉት አመታት ታሪክ ዋስትና ሊሆን አይችልም ”

” በእርግጠኝነት የበላይነታችንን እናስጠብቃለን ” አዲስ ግደይ

” ጨዋታው ደርቢ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ፉክክር ይኖረዋል፡፡ ምንም እንኳ ድቻ አንድ ጨዋታ ቀሪ ቢኖረውም በነጥብ በመቀራረባችን ጥሩ ጨዋታ ይታይበታል፡፡ በእኛ በኩል ለጨዋታው በአይምሮም በአካል ብቃቱም በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡ በሜዳችን በወላይታ ድቻ ላይ ያለንን የበላይነት እሁድ በመድገም በእርግጠኝነት እናሸንፋለን፡፡ ”

” አቻ ለመውጣት አንጫወትም ” አላዛር ፋሲካ

” ጨዋታው ጠንካራ ነው የሚሆነው፡፡ ደርቢ እንደመሆኑ መጠን ጠንካራ እንደሚሆን እገምታለው፡፡ እኛ በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡ የመጣነውም ለማሸነፍ ነው፡፡ ጨዋታው ከሜዳችን ውጭ ቢሆንም አቻ ለመውጣት አስበን አንጫወትም፡፡ እነሱ ጠንክረው እንደሚጠብቁን እናውቃለን ፤ እኛም ጥሩ ሰርተን እናሸንፋለን ብዬ እጠብቃለው፡፡ ”

ግምታዊ አሰላለፍ

በሊጉ በየሳምንቱ እምብዛም ለውጥ የማያሳይ አሰላለፍ ከሚጠቀሙ ክለቦች ሁለቱ ይጠቀሳሉ፡፡ የድቻው መሳይ ተፈሪ በሁለት ጨዋታዎች ከ2 ተጫዋች ለውጥ ውጪ ተመሳሳይ አሰላለፍ ሲጠቀም የሲዳማ ቡናው አለማየሁ አባይነህ ከ3 ጨዋታዎች በሁለቱ ተመሳሳይ በአንዱ የአንድ ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ተጫውቷል፡፡

ሲዳማ ቡና

ለአለም ብርሃኑ

ግሩም አሰፋ – አንተነህ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ወሰኑ ማዜ

ትርታዬ ደመቀ – ሙሉአለም መስፍን – ፍፁም ተፈሪ – አዲስ ግደይ

በረከት አዲሱ – ኤሪክ ሙራንዳ

 

ወላይታ ድቻ

ወንድወሰን ገረመው

ተክሉ ታፈሰ – ሙባረክ ሽኩር – ፈቱዲን ጀማል

ያሬድ ዳዊት – አማኑኤል ተሾመ – በዛብህ መለዮ – ዮሴፍ ድንገቱ – አናጋው ባደግ

አላዘር ፋሲካ – ቴዎድሮስ መንገሻ

ማን ይመራዋል?

ጨዋታውን ፌዴራል አርቢቴር ዳዊት አሳምነው እንዲመራው በፌዴሬሽኑ ተመድቧል፡፡

2 Comments

  1. ke 2006 jemero 2 keleboch miyadergut chewata ameltogn ayawukem enam be estadiyem yemitayu mesemer yesatu negeroch kedegafi mestekakele sinorebet keleboch lemashenefe yalachewu felagot des yasegnal ….degafiyoch wede estedyem yemnegebawu teznaneten lemewutat enji debdeb lemayet selalone …… dele lebuna ….

Leave a Reply