ሪፖርት | ደደቢት በአስራት ኃይሌ እየተመራ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ተካሂዶ ደደቢት ሃዋሳ ከተማን በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች 2-0 መርታት ችሏል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን በሳምንቱ መጀመሪያ ያሰናበተው ደደቢት በአስራት ሃይሌ እየተመራ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል፡፡

ጥቂት ተመልካች በተከታተለው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ እንግዶቹ በኳስ ቁጥጥር እንዲሁም በግብ ሙከራ የተሻሉ ሆነው ታይተዋል፡፡ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ በ10ኛው ደቂቃ የሃዋሳ ከተማው ፍሬው ሰለሞን በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ የሰማያዊዎቹ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አሻቴ በቀላሉ አድኖበታል፡፡ በ24ኛው ደቂቃ አስራት መገርሳ እና ሽመክት ጉግሳ በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ የላኩትን ኳስ ጌታነህ ከበደ በሜንሳ ሶሆሆ መረብ ላይ በማስቆጠር ደደቢትን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኃላ ሃዋሳዎች አምስት ያክል የግብ ሙከራዎችን በተጋጣሚያቸው ላይ ማድረግ ችለዋል፡፡ በ31ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የሞከረውን ሙከራ ጋናዊው ግብ ጠባቂ ክሌመንት መልሶበታል፡፡ ለደደቢት የኃላ መስመር ራስ ምታት የነበረው ፍሬው ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ያገኘውን ጥሩ አጋጣሚ ሳይጠቀምበት የደደቢት ተከላካዮች አውጥተውታል፡፡

picsart_1480790452088

ከዕረፍት መልስ የሃዋሳ ከተማ የበላይነት የቀጠለ ሲሆን በ48ኛው እና 56ኛው ደቂቃ አሁንም ፍሬው ለግብ የቀረቡ ሁለት ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ ሃዋሳ ከተማ ምንም እንኳን የጨዋታ ብልጫ ቢኖረውም ወደ ግብ የሚያደርጉት ሙከራዎች ፍሬ ሳያፈራ የሁለተኛው አጋማሽም ተጠናቅቋል፡፡

ዳዊት ፍቃዱ ተጎድቶ ህክምና አድርጎ ሲገባ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ነፃ መስሎት ለቆመው መሳይ ጳውሎስ ሲያቀብለው ዳዊት ህክምናውን ጨርሶ ወደ ሜዳ በገባበት ቅፅበት ከውኋላው መጥቶ በመንጠቅ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ጌታነህ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ጌታነህ ወደ ጎልነት ቀይሮታል፡

ጌታነህ ከበደ የኮከብ ግብ አግቢነቱንም በአምስት ግቦች መምራት ጀምሯል፡፡ ሃዋሳ ከተማዎች በ89ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞንን በጉዳት በማጣታቸው የባከኑ ደቂቃዎችን በአስር ተጫዋች ለመጨረስ ተገደዋል፡፡

picsart_1480790544976

የአሰልጣኞች አስተያየት

“የበለጠ ስራ እንደሚያስፈልገን በግልፅ ይታያል” የደደቢት አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ

“ጨዋታው የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ እርግጥ እኔ በቴክኒካል ዳይሬክተርነት ነበር ስሰራ የነበረው፡፡ ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ የያዝኩት ማክሰኞ ዕለት ነው፡፡ መጀመሪያ የነበረው ስራ ነው ትንሽ ነገሮች ነው ለማስተካከል የሞከርኩት፡፡ እግርኳስ ውጤት ነው፡፡ ውጤቱ ደግሞ ተገኝቷል፡፡ የበለጠ ስራ እንደሚያስፈልገን በግልፅ ይታያል፡፡ በሂደት እየተስተካከልን እሄዳለን፡፡ ጨዋታው ከጠበቁት በላይ ነው፡፡ ጥሩ የተጫወቱት ማለት እችላለው፡፡ ለእኔ ጥሩ ውጤት ነው፡፡”

“ቡድኑ በተለይ የታክቲካል ዲሲፕሊን ላይ ትንሽ ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ መሃል እና ፊት ላይ ያለው ውህደት ለእኔ ብዙም አላሳመነኝም፡፡ እዚህ ላይ ስራ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ ከኃላም ትንሽ የሚሰሩ ነገሮች ላይ፡፡ በሂደት እያስተካከልን እንሄዳለን፡፡ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው ሙሉ ነው የምትልብት ሂደት ላይ አይደለም ገና ብዙ ስራ ይቀረናል፡፡”

picsart_1480790516245

“መከላከል ላይ መጠነኛ መዘናጋቶች ነበሩብን” የሃዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውብቱ አባተ

“እንቅስቃሴው ሙሉ 90 ደቂቃ መልካም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከጨዋታው ውስጥ ግቦቹን ብታወጣቸው የበለጠውን ድርሻ ተቆጣጥረን መጫወት ችለናል፡፡ ያው ዞሮዞሮ በእግርኳስ ግብ ያገባ ነው የሚያሸንፈው፡፡ ያገኟቸውን ኳሶች እነሱ መጠቀም ችለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ውጤቱን ይዘን መውጣት አልቻልንም፡፡ ልዩነቱ የነበረው እዛጋ ነው ብዬ ነው ማስበው፡፡”

“በእግርኳስ ካለልህ ያገኘኅውን አንድ ኳስ ትጠቀማለህ፡፡ አጋጣሚ ካልፈቀደልህ ደግሞ ብዙ ኳሶችን ታመክናለህ፡፡ ከዕረፍት በፊት ስድስት ወይም ሰባት የማዕዘን ምቶችን አግኝተናል፡፡ ይህ ማጥቃታችንን ነበር የሚያሳየው፡፡ በተቃራኒው እኛ ላይ አንድ ኳስ ብቻ ነበር የተሞከረው፡፡ ሙከራዎቹን ብቻ ካየህ እኛ ላይ የሞከሩት ከሁለት ኳስ በላይ አይሆንም፡፡ ያገኙትን በመጠቀም እነሱ የተሻሉ ነበሩ፡፡ እዛ ላይ መስራት እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ መከላከል ላይ መጠነኛ መዘናጋቶች ነበሩብን፡፡ ጨዋታውን ከመቆጣጠራችን አንጻር የተፈጠረ ነው የሚመስለኝ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *