ናይጄሪያ የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ አሸናፊ ሆናለች

የ2016 ቶታል አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ በካሜሮን አዘጋጅነት ሲካሄድ ቆይቶ ቅዳሜ ያውንዴ ላይ በተደረገ ጨዋታ ናይጄሪያ ካሜሮንን 1-0 በማሸነፍ ለስምንተኛ ግዜ የዋንጫው ባለቤት ሆናለች፡፡ በአፍሪካ የሴቶች እግርኳስ ላይ አሁንም ምዕራብ አፍሪካዊያኑ ሃያልነታቸውን ማስቀጠል የቻሉበት ሆኖ አልፏል፡፡

በ2014 ናሚቢያ ባስተናገደችው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ፍፃሜ የተገናኙት ሁለቱ ሃገራት በ2016 ዳግም ለዋንጫው ተፋጠው ነበር፡፡ በስታደ አማዶ አሂጆ በተካሄደው ጨዋታ የዲዛየር ኦፓራንዚ የ85ኛ ደቂቃ ግብ ናይጄሪያን ለቻምፒዮንነት አብቅቷል፡፡ በጨዋታው አብዛኛው ክፍለ ግዜ ሱፐር ፋልከኖቹ የጠሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡ ካሜሮኖች በበኩላቸው ያገኟቸውን እድሎች ሲያመክለኑ አምሽተዋል፡፡

picsart_1480834054117

ካሜሮን እስከፍፃሜ ባለው ጨዋታ አንድም ግብ ያላስተናገደች ሃገር የነበረች ቢሆንም ለናይጄሪያ ግን እጇን ሰጥታለች፡፡ የናይጄሪያ አሰልጣኝ ፍሎረንስ ኦማግቢሚ በተጫዋችነትም በአሰልጣኝነትም ዋንጫውን ማሳካት የቻለች የመጀመሪያዋ ሰው ሆናለች፡፡

ዓርብ ዕለት ለደረጃ በተደረገ ጨዋታ ጋና ደቡብ አፍሪካን 1-0 አሸንፋለች፡፡ የሊንዳ ኢስሃን የ48ኛ ደቂቃ ግብ ብላክ ኩዊንሶቹን ለድል አብቅቷል፡፡

ናሚቢያ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ፍጻሜ ናይጄሪያ ካሜሮንን 2-0 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡ አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ 10 ግዜ ሲካሄድ ስምንቱን የወሰደችው ናይጄሪያ ናት፡፡ የናይጄሪያዋ ግብ አዳኝ አሲሳት ኦሾአላ በስድስት ግቦች የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆናለች፡፡

Leave a Reply