ታክቲካዊ ትንታኔ ፡ ኢትዮጵያ ቡና 0-1 ኤሌክትሪክ

በሚልኪያስ አበራ

 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግማሽ የውድድር ዘመን ተስተካካይ ጨዋታዎች በተለያዩ ስታድየሞች ተካሂደዋል፡፡ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቀያዮቹ 1-0 አሸንፈው ከ5 ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሸ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለት የተከላካይ አማካዮች የተዋቀረውን 4-2-3-1 የተጨዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን የተገበሩ ሲሆን ኤሌክትሪኮች ደግሞ በሳጥን ቅርፅ የአማካይ ክፍል (Box midfield) የሚታወቀውን 4-2-2-2 ፎርሜሽን ተጠቅመዋል፡፡

(ምስል 1 ፡ ከላይ ያለውን ምስል ይመልከቱ)

 

የቡናዎች የጨዋታ አቀራረብ

በጨዋታው ቡናዎች ከተጠቀሙባቸው ሁለት የተከላካይ አማካዮች (ደረጄ ኃይሉ እና ሐብታሙ ረጋሳ) አንደኛው (ሐብታሙ) በጨዋታው ሒደት በሚፈጠሩ ለውጦች በአብዛኛው ከፊት ካሉት የማጥቃት ባህርይ ያለቸው አማካዮች ጋር ተቀራርቦ በመጫወቱና ደረጄ ደግመሞ ይበልጥ ለተከላካዮች ሽፋን የመስጠት ኃላፊነት ላይ በማተኮሩ ቡድኑ 4-1-4-1 ን የሚተገብር የሚመስልባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡

እነዚህ ሁለት የ6 ቁጥር ሚናን የሚወጡ አማካዮች በሜዳው ቁመት ከኋላ እና ከፊት ሁነው መታየታቸው የቡናን በጎንዮሽ (double Pivot ጎን እና ጎን) የሚኖረውን የመከላከል ጥንካሬ ቢቀንሰውም በማጥቃቱ ረገድ ግን የተሻለ እንዲንቀሳቀስ ሲያደርገው ተስተውሏል፡፡ የመስመር ተከላካዮች (አህመድ ረሺድ እና ሳሙኤል ወንድሙ) ተደጋጋሚ የፊት ለፊት ሩጫ (Overlapping movement) ቀጥተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያለው ቢሆንም በተዘዋዋሪ በመስመር ላይ የሚፈጠረውን ክፍተትም እንዲሸፍኑ ሲያግዛቸው ታይቷል፡፡

ተጋጣሚያቸው ኤሌክትሪክ በመሃል ክፍል ላይ የነበረው የተጨዋቾች የቦታ አያያዝ (Positioning) በሁለቱም መስመሮች ቡናዎች ነፃ ሁነው እንዲንቀሳቀሱ እና ሰፊ የመጨወቸቻ ክፍተትም እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ኤሌክትሪክ በመሃል ክፍል የጠበበ እና በሁለት መስመር (ባለሁለት ተጨዋቾች መስመር) የተደረደሩ አራት ተጫዋቾች ያሳተፈ የሳጥን ቅርፅ ያለው የአማካይ ክፍል (Box Midfield) መጠቀሙ ለተጋጣሚ ሙሉ በሙሉ ከተከላከዮች ፊት ለፊት ያለውን ሰፊ ክፍተት (space) ፉልባኮችን እንዲሸፍኑት ሲያስገድዳቸው ነበር፡፡ በጨዋታው የቡናው ኤልያስ በማጥቃተ አጨዋወት (attacking Phase) አማካይ ክፍሉን እና አጥቂውን ቢንያም አሰፋን በማገናኘት ስራ ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ የታየ ቢሆንም በይበልጥ ኳስን ለመቀበል እና የተጋጣሚን የመሃል ሜዳ የቁጥር የበላይነት ተፅእኖ ለመቀነስ ወደኋላ እያፈገፈገ ከሁለቱ የመሃል ተከላካዮች በመቅረብ መደበኛ ጎነ ሶስት (triangle) ምስል ያለው ቅርፅ በመስራት የመቀባበያ አማራጮችን ሲያበዛም ነበር፡፡ ቢንያምም በሁለቱ መስመሮች እየተገኘ የማጥቃት ማእዘናትን ማስፋትና የተጋጣሚን የመስመር ተከላካዮች የፊት ለፊት እንቅስቃሴ መጠነኛ በሆነ መልኩ መግታት ችሏል፡፡ ቡናዎች ብዙም አደገኛ ያልሆኑ የግብ ሙከራዎች በመጀመርያው 45 ቢያደርጉም ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም፡፡ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ደረጄ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ (through ball) ለአስቻለው ቢልክለትም የቀኝ መስመር አማካዩ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አሰግድ አክሊሉ አድኖበታል፡፡ ተጋጣሚ የሚፈጥረውን ሰፊ ክፍተት ያለመጠቀም ችግር የአብዛኛው የሊጉ ቡድኖች ባህርይ ቢሆንም ከኤሌክትሪክ ጋር የሚጋጠሙ ቡድኖች በመስመሮች የሚገኘውን ነፃ እና ሰፊ ቦታ በመስመር አማካዮቻቸወው ሊጠቀሙ አለመቻላቸው የሚያስገርም ነው፡፡ ቡና ጨዋታውን ወደ ግራው መስመር እያደላ እና ተጫዋቾችን በአንድ መስመር (በመስኡድ በኩል) በማብዛት (overcrowding) መጫወቱ ለኤሌክትሪኮቸች የመከላከል አጨዋወት አመቺ አና ተገማች እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በቀኝ መስመር ሰፊ ክፍተት እያለ (በአስቻለው ግርማ በኩል) የግራውን መስመር ያን ያህል ብቸኛ የማጥቃት አማራጭ ማድረጋቸው የጨዋታውን ሚዛን ወደ ግራ እንዲያዘነብል አድርጎታል፡፡ ( አንዳንድ በስታድየሙ የተገኙ የቡና ደጋፊዎች ይህን ተደጋጋሚ አጋጣሚ ‹‹ ጥላ ፍለጋ የፈጠሩት አጨዋወት ነው›› ሲሉ ቀልደዋል፡፡ )

(ምስል ሁለት)

bunna 0-1 electric (2)

የኤሌክትሪክ 4-2-2-2

የኤሌከትሪኮች ‹‹Magic Rectangle›› / ‹‹Magic square ›› ተብሎ የሚጠራውን ይህን አጨዋወት ሲጠቀሙ የመጀመርያቸው አይደለም፡፡ በሁለት ከሳጥን ሳጥን በሚመላለሱ እና በሁለት ወደኋላ ያፈረፈጉ የማጥቃት አማካዮች (Deep lying forwards) የተዋቀረው የመሃል ክፍላቸው የመሃል ሜዳ የቁጥር ብልጫ ቢያስገኝላቸውም ከፉልባኮቹ ፊት ለፊት ሰፊ ክፍተትን የመተው ‹‹ ሪስክ ›› እንዲወስዱ አድርጓቸዋል፡፡ ቡናዎች አልተጠቀሙበትም እንጂ፡፡

ፎርሜሽኑ ለመሃለኛው ክፍል አጨዋወት Dynamism ፍሰት ያለውን እንቅስቃሴ ከመጨመሩም በላይ ሚዛናዊ የሆነ ተጨዋቾች የሜዳ ላይ የመጫወቻ ስፍራ እና አቅጣጫ ሰርጭትን ይሰጣል፡፡ ሆኖም ኤሌክትሪኮች ወደ ቀኝ መስመር ባዘመመው አጨዋወታቸው የቀኝ ክፍላቸውን ክፍት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ከመስመር አማካዮች በኃይሉ እና ፍቅረየሱስ በተሻለ አጥቂዎቹ (ራምኬል እና ፒተር) የሜዳውን ስፋት ሲጠቀሙ (width ሲሰጡ) እና የቡናን ፉልባኮች (አህመድ እና ሳሙኤልን) ሲያፍኑ (stifle ሲያደርጉ) ታይተዋል፡፡

የመስመር ተከላካዮቼ (አሳልፈው እና አወት) ረጃጅም የጎንዮሽ ቅብብሎችን (diagonal passes) ሲያደርጉ የነበሩትም ጨዋታ ወዳለበት አቅጣጫ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ አሳልፈው ኳስን ይዞ ወደፊት ቢሄድም ከፊቱ የሚያግዘው የመስመር አማካይ ስለማይኖር በአጨዋወት ዘይቤያቸው የተነሳ ይመስላል ምንም ሳይፈጥር ይመለስ ነበር፡፡ የሁለቱ የተከላካይ አማካዮች የማጥቃት እንቅስቀቃሴ መጠነኛ የነበረ ቢሆንም 37ኛ ደቂቃ ላይ ዊሊያም ኤሳጆ ከሩቅ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ጌቱ ተስፋዬ የመለሰበት ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት የመጀመርያው 45 የኤሌክትሪኮች የግብ ሙከራ ነበር፡፡

የቡናው ደረጀ ይበልጥ ለተከላካዮች ቀርቦ መጫወቱና ሐብታሙ በአብዛኛው በማጥቃት ከልሉ በተደጋጋሚ በመገኘቱ የመብራት አማከዮች በመሃለኛው ክፍል ሰፋ ያለ ቦታን እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡

(ምስል 3)

bunna 0-1 electric (3)

ከእረፍት መልስ ፡ የአጥናፉ ስኬተማ የታክቲክ ለውጥና የቡና 3-4-3/3-1-3-3

ኤሌክትሪኮች በመጀመርያው አጋማሽ የተጠቀሙበትን የጨዋታ አደራደር ቀይረው ሁለተኛው አጋማሽ በ4-2-3-1 ፎርሜሽን ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ ይህም ቡድኑ በመስመር ላይ የነበረውን የመከላከል እና የማጠጥቃት እንቅስቃሴ የተሸለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ አጥቂው ራምኬል ወደ ግራ መስመር አዘንብሎ እንዲጫወት በኃይሉ ደግሞ ‹‹የ10 ቁጥር›› ሚናን እንዲወጣና ፍቅረየሱስ ወደ ቀኝ መስመር አዘንብሎ የአህመድን የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲገታ ተደርጓል፡፡

ይህም ኤሌክትሪኮችን ተደጋጋሚ የማጥቃት ጫና እና የግብ ሙከራዎችን ከመጀመርያው አጋማሽ በተሸሸለ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡ በአጥቂዎቹ ተደጋጋሚ የቦታ ቅይይርም በግራው መስመር ዊሊያም ፣ በኃይሉ እና ራምኬል ኦቨርሎድ በማድረግ የቡናዎችን ትኩረት ወደዚህኛው መስመር እንዲያጋድል ሲያደርጉ ነበር፡፡ በ63ኛው ደቂቃ ላይም በቡና አማካዮች ወደኋላ የተመለሰን ኳስ አሳልፈው መኮንንነ ኦቨርላፕ በማደረግ ለፒተር አቀብሎ ግዙፉ አጥቂ ኳስን ከመረብ ሊያዋህድ ችሏል፡፡ ቡድኑ በመከላከልም ረገድ በይበልጥ ጥካራ ሆኖ መቅረቡ (በተለይ በቀኝ ክፍሉ) ውጤትን አስጠብቆ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተጫዋቾች እና የፎርሜሽን ለውጥ አድርገው ነበር፡፡ ዮናስ ገረመው እና አበኮዬ ሻኪሩን በቀኝ ፉልባኩ ሳሙኤል ወንድሙ እና አማካዩ መስኡድ ቀይሮ በማስገባት እንዲሁም በግራ መስመር አማካይ የነበረው አህመድን 3ኛ የመሃል ተካላካይ በማድረግ ወደ 3-4-3 /3-1-3-3 የተጠጋ አደራደር መጠቀም ጀመሩ፡፡ ኤሌክትሪኮች በተሻለ ክፍት የመጫወቻ መስመሮቻቸውን በመዝጋታቸው ቡናዎች ክፍተት የሚያገኙበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ቡናዎች ቀድመው በመጀመርያው አጋማሽ የተጋጣሚን ደካማ ቀጠና (weaker zone) አለመጠቀማቸው የኋላ ኋላ ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ የመብራቶች ኳስን ያማከለ የመከላከል እንቅስቃሴ (ball oriented defending movement) ይበልጥ የቡናዎች የማጥቃት አጨዋወት እንዲመክቱ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ውጤቱን አስጠብቀው ጨዋታውን ጨርሰዋል፡፡

(ምስል 4)

bunna 0-1 electric (4)

ያጋሩ