የጨዋታ ሪፖርት | የደቡብ ደርቢ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት የደቡብ ደርቢ ይርጋለም ላይ ወላይታ ድያን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻን በአዲስ ግደይ ብቸኛ ጎል በማሸነፍ በሜዳው በወላይታ ድቻ ያለመሸነፍ ክብሩን አስጠብቆ ወጥቷል፡፡

ለወትሮው ሁለቱ ቡድኖች በሚገናኙበት ጨዋታ ከፍተኛ ተመልካች ፣ ውጥረት እና የማሸነፍ ፍላጎት የሚኖር ሲሆን ዛሬ በይርጋለም ሁለገብ ስታድየም የታየውም ይኸው ነበር፡፡

የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ቡድናቸውን ለመደገፍ ወደ ስቴዲዮሙ መትመም የጀመሩት ገና ከማለዳ ጀምሮ ነበር ። ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል የወላይታ ድቻ ደጋፊዎችም ክለባቸውን ለመደገፍ በስቴዲዮም ታድመው ነበር፡፡

picsart_1480874639434

የዕለቱ አልቢትር ፌደራል ዳኛ ዳዊት አሳምነው የጨዋታውን መጀመር የፊሽካቸው ድምፅ ካሰሙበት ሰአት አንስቶ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ከፍተኛ ጫና በመፍጠር በአዲስ ግደይና በትርታዬ ደመቀ አማካኝነት በተደጋጋሚ የወላይታ ድቻን የኋላ መስመር የፈተሹ ሲሆን ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ ወላይታ ድቻዎች ጨዋታውን ለማቀዝቀዝ በሚመስል መንገድ የተለያዩ ቴክኒኮችን ተጠቅመው ጨዋታውን አረጋግተውታል፡፡ በዚህም በዛብህ መለዮ በ39ኛው ደቂቃ ካደረገው የጎል ሙከራ ውጪ እምብዛም የተለየ ነገር ሳይታይ የመጀመርያው አጋማሽ ያለጎል ተጠናቋል፡፡

picsart_1480874704205

በሁለተኛው አጋማሽ ኬንያዊው አንጋፋ ኤሪክ ሙራንዳ ተቀይሮ ከገባ በኋላ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ መሆን ችሏል፡፡  ሲዳማ ቡናም ሙሉ በሙሉ ጨዋታውን ተቆጣጥሮ የተጫወተ ሲሆን በተለይ 63 እና 71ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይና ኤሪክ ሙራንዳ የሞከሯቸውና የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው ኳስ ለብልጫቸው ማሳያ ነበሩ፡፡

ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሲዳማዎች ጥረታቸው በ79ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ ኤሪክ ሙራንዳ በቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አዲስ ግደይ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት የሲዳማን ወሳኝ የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በዝምታ ተውጦ የነበረው ስታድየምም በደጋፊዎች ጭፈራ ተንጧል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ወላይታ ድቻ የአቻነች ግብ ለማግኘት በዛብህ መለዮ እና ዳግም በቀለ አማካኝነት ሙከራዎች ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ጨዋታውም በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

picsart_1480874480089

አለማየሁ አባይነህ

” የቡድኔ እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር፡፡ ብልጫ እንደመውሰዳችን ከአንድ በላይ ጎል አስቆጥረን ማሸነፍ ይገባን ነበር፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ላይ የነበሩብንን ክፍተቶች አርመን የአጥቂ አማራጫችንን አስፍተን ኤሪክ ሙራዳን በማስገባት ያደረግነው ቅያሪ ተሳክቶልን ጨዋታውን በሚገባ ተቆጣጥረን አሸንፈን ወጥተናል፡፡ በሜዳችን ያለመሸነፍ ጉዟችንን ከአሁን በኋላም አስጠብቀን እንቀጥላለን ። በጨዋታው ላይ ድንቅ አቋሙን ላሳየኝ አዲስ ግደይ አከብሮቴ የላቀ ነው ”

picsart_1480874528446

መሳይ ተፈሪ

” ማንንም መውቀስ አልፈልግም፡፡ ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ለአሸናፊው ቡድን እንኳን ደስ አላቹ ማለት እፈልጋለው፡፡ ለቀጣይ ጨዋታም የዛሬው ሽንፈት ምንም አይነት ተፅዕኖ ያደርግብናል ብዬ አላስብም፡፡ በቀጣዩ ጨዋታ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን፡፡ ”

 

3 Comments

  1. Soccerethiopia ጫዎታውን በቀጥታ ሲተላለፍ በጣም እናመሰግናለን.ወላይታ ዲቻ በቀጣዩ ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ይመለሳለ፡፡

  2. ጨዋታዉ በስፖርታዊ ጨዋነት መጠናቀቁ ደሰ ይላል

Leave a Reply