የጨዋታ ሪፖርት | ፋሲል የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታ በድል ተወጥቷል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲከናወኑ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረዉ የፋሲል ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በባለ ሜዳዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

9:00ሰዓት የጀመረው ጨዋታ በአስደናቂ የደጋፊ ድባብ ሲከናወን ፋሲል ከተማዎች በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ የሜዳ ላይ ጨዋታ በደጋፊያቸው ታጅበው ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል፡፡

ጨዋታዉ ከመጀመሩ በፊት የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች ለአዳነ ግርማ የማስታወሻ ስጦታ ሲያበረክቱ የደጋፊ ማህበሩም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ሲያደርጉላቸው ተስተወሏል፡፡

በጨዋታው ፋሲል ከተማዎች በሜዳ ላይ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ያገኙዋቸውን የግብ እድሎች በመጠቀም ረገድ ክፋተት ነበረባቸዉ፡፡  ጨዋታው በተጀመረ በ12ኛ ደቂቃ ሳላዲን ሰኢድ የፋሲል ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ዮሃንስ ሽኩር አለመግባባትን ተጠቅሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ ፋሲሎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ጠንካራ ሙከራ ለማድረግ 20 ደቂቃዎች ፈጅቶባቸዋል፡፡ አብዱራህማን ሙባረክ በ32ኛው እና 34ኛው ደቂቃ የሞከራቸው ኳሶች የሮበርት ኦዶንካራ ጥረት ታክሎባቸው ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የመጀመርያው 45 ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ደቂቃ ፋሲሎች የሞከሩት ሙከራ በተከላካዮች ሲመለስ ከ1 ጨዋታ ቅጣት የተመለሰው አብዱራህማን ሙባረክ አግኝቶት አፄዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

በሁለተኛው ግማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተስፋዬ አለባቸው ፣ ፋሲሎች በአብዱራህማን ሙባረክ አማካኝነት ያደረጓቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን ከሳቱ ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

በ87ኛው ደቂቃ ቶጓዊው አጥቂ ኤዶም ሆሶውሮቪ በቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ተጠልፎ በመውደቁ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ኤዶም መትቶ ፋሲልን ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ ያስቻለችውን ኳስ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጨዋታውም በፋሲል ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የፋሲል ደጋፊዎች ደስታቸውን በመላዉ ከተማዋ ሲገልፁ አምሽተዋል፡፡

—-
የጨዋታውን እንቅስቃሴ እና ድባብ የሚገልጹ ፎቶዎችን በዘገባው ለማካተት ያደረግነው ጥረት በኢንተርኔት መዘግየት ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Leave a Reply