ትላንት የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ዛሬ በተካሄዱ 7 ጨዋታዎች ቀጥሏል፡፡ ፋሲል ከተማ ማስገረሙን ሲቀጥል መከላከያ እና አርባምንጭ የመጀመርያ 3 ነጥባቸውን አሳክተዋል፡፡
ጎንደር ላይ ከ9 የውድድር ዘመናት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በሜዳው ጨዋታ ያደረገው ፋሲል ከተማ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሳላዲን ሰኢድ የ12ኛ ደቂቃ ግብ ቀዳሚ ቢሆንም ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸው በፊት ከቅጣት የተመለሰው አብዱራህማን ሙባረክ ፋሲልን አቻ አድርጓል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ደግሞ ዳሽንን ለቆ አፄዎቹን የተቀላቀለው ኤዶም ሆሮሶውቪ ራሱ ላይ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይሮ ፋሲልን አሸናፊ አድርጓል፡፡ ፋሲል በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በመርታት ድንቅ የፕሪሚየር ሊግ ጅማሮ ማድረግ ችሏል፡፡
አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ጅማ ከተማን 3-0 በማሸነፍ የመጀመርያ 3 ነጥቡን አሳክቷል፡፡ ወድሜነህ ዘሪሁን የጅማ ተከላካዮችን አልፎ በመግባት በ33ኛው ደቂቃ የአዞዎቹን ቀዳሚ ግብ አስቆጥሯል፡፡ አምበሉ አማኑኤል ጎበና በ38ኛው ደቂቃ ከተካልኝ ደጀኔ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ የአርባምንጭን መሪነት ወደ 2 ሲያሰፋ ከእረፍት መልስ ተካልኝ ደጀኔ ከታደለ መንገሻ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የአርባምንጩ ዋና አሰልጣኝ ዻውሎስ ፀጋዬ በደጋፊው ተቃዉሞና በክለቡ አመራር ውሳኔ ቡድናቸውን በቴክኒካል ኤሪያ ላይ ሳይመሩ የቀሩ ሲሆን ይህም አሰልጣኙ ሊሰናበቱ ይችላሉ የሚሉ ግምቶችን አጠናክሯል፡፡ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ምትክም በተጫዋችነት እና ረዳት አሰልጣኝነት ቡድኑን እያገለገለ ያለው በረከት ደሙ ጨዋታውን መርቷል፡፡
ድሬደዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 1-0 በመርታት ወደ አሽናፊነት ተመልሷል፡፡ መድንን ለቆ ድሬያዋ ከተማን ዘንድሮ የተቀላቀለው ሐብታሙ ወልዴ በ12ኛው ደቂቃ ከበረከት ይስሀቅ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ድሬዳዋን 3 ነጥብ አስጨብጧል፡፡
መከላከያ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ 3 ነጥብ ባሳካበት ጨዋታ ወልድያን 2-0 አሸንፏል፡፡ ምንይሉ ወንድሙ በ26ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ሲቀይር የመስመር አጥቂው ማራኪ ወርቁ በ62ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሏል፡፡
አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል፡፡ 1-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ያቡን ዊልያም ከመቀመጫ ወንበር ተነስቶ በ53ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ሲያደርግ ዘንድሮ የተለመደው የተከላካይ ቦታውን ትቶ በአጥቂነት እየተሰለፈ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲም በ83ኛው ደቂቃ ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል፡፡
ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ነጥቡን ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አስተካክሏል፡፡ የሲዳማን ወሳኝ የድል ግብ በ79ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው አዲስ ግደይ ነው፡፡
በ4ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፒተር ኑዋዲኬ በቀድሞ ክለቡ ላይ ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ ቢሆንም ዳዊት እስጢፋኖስ በፍጹም ቅጣት ምት ኤሌክትሪክን አቻ አድርጓል፡፡
ትላንት በተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ደደቢት በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች ታግዞ ሀዋሳ ከተማን 2-0 አሸንፏል፡፡