የጨዋታ ሪፖርት | የአዲስ አበባ ስታድየም የትላንት ውሎ. . .

በአራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ቀን ውሎ አዲስ አበባ ስታድየም ሁለት ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ በ9፡00 መከላከያ ወልዲያን 2-0 ያሸነፈ ሲሆን በመቀጠል ኢትዮጽያ ንግድ ባንክ እና ኤሌክትሪክ ባደረጉት ጨዋታ 1-1 ተለያይተዋል።

 

መከላከያ 2-0 ወልዲያ

በወልዲያዎች የሜዳ ክልል ላይ ባመዘነው የመጀመሪያ ግማሽ የጨዋታ ሂደት ገና በ2ኛው ደቂቃ ነበር ሳሙኤል ታዬ ሶስት የወልድያ ተከላካዬችን አልፎ በሞከረውና በሳተው ኳስ ጨወታው በተሟሟቀ መልኩ የጀመረው። ከዚህም በኃላ በ26ኛው ደቂቃ በምንይሉ ወንድሙ አማካይነት መከላከያዎች የመጀመሪያውን ጎል እስኪያስቆጥሩ ድረስ በነበሩት ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ለማየት ተችሏል ። በዚህም መሰረት ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ወደግብ ይደርሱ የነበሩት መከላከያዎች ከቆሙ ኳሶች በመነሳት በምንይሉ ወንድሙ እና በበሀይሉ ግርማ አማካይነት በግንባር በመግጨት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።

በመልሶ ማጥቃት ወደተጋጣሚያቸው ሜዳ ለመግባት ይሞክሩ የነበሩት ወልዲያዎችም ጥቂት ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይም በሶስተኛው ደቂቃ ያሬድ ሀሰን በቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት የሞከረው እንዲሁም 15ኛው ደቂቃ ላይ ከመከላከያ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ጠርዝ ላይ ጫላ ድሪባ በቀጥታ ወደግብ የሞከረው ኳስ የሚጠቀሱ ቢሆንም በሁለቱም አጋጣሚዎች የተሞከሩት ኳሶች ሀይል ስላልነበራቸው በቀላሉ ከ3 ወራት ጉዳት በኋላ የመጀመርያ ጨዋታውን ባደረገው ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ተይዘዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ወደፊት ገፍተው የተጫወቱ ሲሆን መከላከያዎች በበኩላቸው መሪነታቸውን ለማስጠበቅ ጠንቀቅ ብለው መጫወትን መርጠዋል። ያም ቢሆን በ62ኛው ደቂቃ ላይ አንዷለም ንጉሴ በረጅም የተላከለትን ኳስ በደረቱ ሲያበርድለት ጫላ ድሪባ ወደጎል ሲመታው እና በተከላካዮች ሲመለስ ምንያህል ይመር አግኝቶ በቀጥታ ከሞከረውና ወደላይ ከተነሳው ኳስ በቀር ወልዲያዎች በሚፈለገው መጠን የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም ነበር።

መከላከያዎች በበኩላቸው በ56ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ታዬ በቀኝ በኩል ወደ ወልዲያዎች የግብ ክልል በመቅረብ ከሞከረው ኳስ በኃላ በ62ኛው ደቂቃ ላይ በሰነዘሩት የመልሶ ማጥቃት የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው ምንይሉ ወንድሙ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ማራኪ ወርቁ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ወደሁለት ከፍ አድርጎታል። በተቀረውም ጊዜ ውጤታቸውን በማስጠበቅ የአመቱን የመጀመሪያ ድላቸውን ማስመዝገብ ችለዋል።

ለሁሉም ቡድኖች እኩል እንደሚዘጋጁ እና ለዚህኛውም ጨዋታ የተለየ ዝግጅት አለማድረጋቸውን የተናገሩት የመከላከያው አሰልጣኝ ሻምበል በለጠ ገ/ኪዳን ስለ ድሉ አስተያየተቸውን ሲሰጡ ” ጨዋታውን አሸንፈናል በማሽነፋችንም ደስ ብሎኛል ። ከዚህ በላይ ጥሩ አጋጣሚዎች ነበሩን እና ከዚህ በላይ ጎሎችን ማግባት ነበረብን። ነገር ግን ከምንም በላይ ከሽንፈት በመምጣታችን ዛሬ ማሸነፋችን ጥሩ ነው። ጨዋታውን ማሸነፍ ለኛ ግዴታ ነበር ተጨዋቾቹ ላይ ያየነው መነሳሳትም ደስ ሚያሰኝ ነበር። ” ብለዋል።

ሻምበል በለጠ ቀጥለውም አሰልጣኙ ስለቡድኑ የስካሁኑ አጠቃላይ አቋም ሲናገሩ ” ውድድሩ ገና መጀመሩ ነው። እኛም በሊጉ እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይም ጭምር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራን ነው ።” በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።

የተሸናፊው ወልዲያ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በበኩላቸው ” በዛሬው ጨዋታ ቡድናችን ጥሩ አልነበረም። አየሩም ትንሽ ነፋሻማ ስለነበረ እና ከዛ በተጨማሪም በመጀመሪያው ግማሽ የተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ልጆቻችንን ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል። በተረፈ ግን አዲስ አበባ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታችን እንደመሆኑ መጠን ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።” በማለት ጨዋታውን የገለፁት ሲሆን የቡድናቸውን አጠቃላይ አቋምም ሲመዝኑ ” በመጀመሪያዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነበር። ዛሬ ግን ትንሽ ወረድ ብለናል። እንደ አጨራረስ ችግር ያሉ ያየናቸው ክፍተቶች አሉ። እነዛን አስተካክለን ለቀጣይ ጨዋታዎች ጠንክረን እንቀርባለን። ” ብለዋል። በተጨማሪም በጨዋታው የተሰጠባቸውም ፍፁም ቅጣት ምት ተከትሎ በዳኝነቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሲሰጡ ” በዳኝነቱ ዙሪያ ይሄ ነው ብለን ምንለው ነገር የለም። ዳኝነትን ከነስህተቱ ነው ምንቀበለው ። በተረፈ ግን እኛ ራሳችን ጥሩ አልነበርንም ” በማለት ነበር።

picsart_1480880681320

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 ኤሌክትሪክ

 

እንደእለቱ የአየር ሁኔታ በቀዘቀዘ መልክ የጀመረውና እንደተቀዛቀዘ የተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በመሀል ሜዳ ላይ በተደጋጋሚ በሚቆራረጡ ኳሶች እና በጥቂት የጎል ሙከራዎች የታጀበ ነበር።

በንፅፅር የተሻሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች የተሻሉ ሙከራዎችን ሲያረጉ በተለይም በ8ኛው ደቂቃ ከሙላለም ጥላሁን የተቀበለውን ኳስ ኢብራሂም ፎፋኖ ከቀኝ በኩል ወደግብ አክርሮ ሲመታ ፍፁም ገ/ማርያም በመንሸራተት ለማስቆጠር ሞክሮ ሳይሳካለት ኳሷ በግቡ የግራ ቋሚ የወጣችበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነው ። ከዚህ በተጨማሪም በእለቱ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ሙሉአለም ጥላሁን በ41ኛው ደቂቃ ከንግድ ባንክ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን አቅራቢያ በቀጥታ የሞከረውና ኢማኑኤል ፌቮ ያዳነበት ኳስም ሌላው የቡድኑ ጥሩ ሙከራ ነበር።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው በ26ኛው ደቂቃ አምሀ መስፍን በረጅም የተላከውን እና የኤሌክትሪክ ተከላካዮች በአግባቡ ያላራቁትን ኳስ አግኝቶ ወደግብ ሲሞክር የግቡን የግራ መረብ ታኮ የወጣበትን አጋጣሚ ከመፍጠራቸው በቀር ሌላ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳያረጉ ነበር የመጀመሪያው ግማሽ የተጠናቀቀው።

የጨዋታው አነጋጋሪ ክስተት የተፈጠረው ከእረፍት መልስ በ48ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በእለቱ የመሀል ተከላካይ ሆኖ የተሰለፈው ተስፋዬ መላኩ በእግር የሰጠውን ኳስ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ኤቡ ሱሊማን በእጅ በመያዙ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከኤሌክትሪክ ግብ ጥቂት ሜትሮች ርቆ ሁለተኛ ቅጣት ምት ያገኛሉ ፤ ይህ አጋጣሚ የተወሰነ ክርክር በተጨዋቾች እና በዳኞች መሀል ቢያስነሳም ዋናው ጉዳይ ግን የተፈጠረው በሁለተኛው አጋማሽ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀንን ቀይሮ የገባው ግዙፉ አጥቂ ፒተር ንዋድኬ የተሰጠውን ሁለተኛ ቅጣት ምት በቀጥታ መቶ ሲያስቆጥር ነው። የመሀል ዳኛውም ግቧን ሳያፀድቁ ቀርተው ረዳት ዳኛውን ካናገሩ በኃላ ግን ጎሏን አፅድቀዋታል። የኤሌክትሪክ ተጨዋቾችም ኳሱ በሌላ ተጨዋች ሳይነካ በቀጥታ መመታት አልነበረበትም በማለት ባነሱት ጥያቄ ጨዋታው እስከ 53ኛው ደቂቃ ድረስ ተቋርጦ ቆይቷል። በመጨረሻም ኤሌክትሪኮች ክስ ካስመዘገቡ በኃላ ነበር ጨዋታው የቀጠለው።

ከዚህ በኃላ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ኤሌክትሪኮች በ75ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ሲራጅ በሙላለም ጥላሁን ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ አስቆጥሮ አቻ ከመሆናቸው ባለፈም በ59ኛው ደቂቃ በኢብራሂም ፎፋኖ እንዲሁም በ79ኛው ደቂቃ በፍፁም ገ/ማሪያም አማካይነት የጎል ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ጎል ሳያስቆጥሩ ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨወታው መጠናቀቅ በኃላ የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዬ በሰጡት አስተያየት ” ጨዋታው ተመጣጣኝ ነበር ማለት ይቻላል። ሁለቱም ቡድኖች ኳስን መሰረት አርገው ነበር የተጫወቱት፡፡ በመሆኑም ክፍት የሆነ ጨዋታ ነበር። ተጨዋቾቼ ኳስን ይዘው እንዲጫወቱ ነበር የፈለኩት ያሰብኩትንም ነገር በመተግበራቸው ደስተኛ ነኝ።”  ሲሉ ስለ 48ኛው ደቂቃ ትዕይንት ለተጠየቁት ጥይቄም “የተሰጠብን ሁለተኛ ቅጣት ምት ነው ። ዋና ዳኛው ከመስመር ዳኛው ይልቅ ለኳሱ ቅርብ ነበር ። በማየቱም የሰጠውን ውሳኔ ረዳት ዳኛውን ከጠየቀ በኃላ ነው የቀየረው። መጠየቅም አይገባውም ነበር ብዬ አስባለው። ነገር ግን ይሄ የዳኛው ውሳኔ ስለሆነ መቀበል የግድ ነው ።  በርግጥ ክስ አስይዘናል ሆኖም ግን የጨዋታው አንዱ ክፍል ስለሆነ ውጤቱን ያስለወጠ ክለብ እስከዛሬ የለም፡፡ እኛም የሆነውን ነገር ተቀብለናል።” ሲሉ መልሰዋል።

የጨወታውን ውጤት ተከትሎ በሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማሪያም በበኩላቸው ” ሁለት ጨዋታዎችን ከሜዳችን ውጪ አድርገናል፡፡ የገጠምናቸውም ቡድኖች በደጋፊያቸው ፊት መጫወታቸው እና ጥሩ ብቃትና ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ያካተቱ ስለነበሩ ነጥብ ይዘን ለመምጣት ተቸግረን ነበር ። በዛሬውም ጨዋታ ተሸንፈን ከመምጣታችን እና ኤሌክትሪክ ካለው የተጨዋቾች ጥራት እና ጥንካሬ አንፃር ያደረግነው ፉክክር ጥሩ ነበር፡፡ ወጤቱም ተገቢ ነው።” በማለት ስለጨዋታው የነበራቸውን ሀሳብ ሲሰጡ ስለተቆጠረባቸው የፍፁም ቅጣት ምት አግባብነት ተጠይቀውም ሲመልሱ ” በኔ እይታ ርቀት ስላለው ይሄ ነው ብዬ ለመገመት አልችልም፡፡ ቢሆንም በዳኝነት ዙሪያ ብዙ መናገር አልፈልግም፡፡ ዳኛው በቅርበት ስላለ ለሱ ይበልጥ ይታየዋል። እግር ኳስ ደግሞ በአንድ አጋጣሚ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ እኛም የምናገኛቸውን እድሎች መጠቀም አለብን፡፡ ስለዚህም በዳኛ ማሳበብ አልፈልግም ፤ ከነስህተቱ መቀበል መቻል አለብን። ” ብለዋል። በመጨረሻም አሰልጣኙ በብድኑ ጥሩ አቋም ላይ ያለመገኘቱን ችግር ምክንያት ሲያብራሩ ” የክለባችን ስብስብ ዘንድሮ አርኪ አይደለም። አንድ ቡድን በየቦታው ተመጣጣኝ የሆኑ ሁለት ሁለት ተጨዋቾች ሊኖሩት ይገባል። ከፊታችን ብዙ ተደራራቢ ጨዋታዎች  ከመኖራቸው አንፃር የስኳድ መመናመን እንዳይገጥመን ስጋት አለኝ። አስራ አራት ተጨዋቾች ከስር አድገዋል፡፡ አምና የለቀቁት አስር ተጨዋቾች ናቸው። ወደቡድኑ  ያስገባናቸው ሦስት ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ወደ አስራ አንድ ሚሆኑ ተጨዋቾች ልናገኝ እንችላለን፡፡ በዚህ ብቻ ግን አመቱን ሙሉ መዝለቅ አይቻልም ፤ በጣም ከባድ ስለሆነ። ቢሆንም ግን የክለቡም የኔም አቋም በሊጉ ላይ ለመቆየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ነው።” ብለዋል።

Leave a Reply